በእስራኤል የሽብር በተባለ ጥቃት ሦስት ሰዎች ተገደሉ

ይህንን ጥቃት የፈጸሙ ሰዎችን ፖሊስ እያደነ ሲሆን መንገዶች ተዘግተው በየተሽከርካሪው ፍለጋ እየተካሄደ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ይህንን ጥቃት የፈጸሙ ሰዎችን ፖሊስ እያደነ ሲሆን መንገዶች ተዘግተው በየተሽከርካሪው ፍለጋ እየተካሄደ ነው።
ታትሟል

በማዕከላዊ እስራኤል ኢላድ በተሰኘችው ከተማ ፖሊስ ሽብር እንደሆነ በጠረጠረው ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል።

በቢላና ቀስት ፓርክ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ላይ የተሰነዘረውን ይህንን ጥቃት ሁለት ሰዎች እንደፈጸሙት የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

እስራኤል የተመሠረተችበት ቀን በሚዘከርበት ዕለት ላይ የተፈጸመውን ይህንን ጥቃት የፈጸሙ ሰዎችን ፖሊስ እያደነ ሲሆን መንገዶች ተዘግተው በየተሽከርካሪው ፍለጋ እየተካሄደ ነው።

በስፍራው በበጎ ፍቃደኝነት ሲያገለግል የነበረ የሕክምና ባለሙያ ክስተቱ "ከልቤ ውስጥ የማይጠፋ" ነው ብሏል።

"ንጹህ አየር ለማግኘት ወደ ፓርክ የሄዱ ሰዎች በሚዘገንን ሁኔታ ሕይወታቸውን አጥተዋል" ሲል ለጀሩሳሌም ፖስት ተናግሯል።

የአይሁድ ኦርቶዶክስ አማኞች የሚበዙባት የኢላድ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳያወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የእስራኤሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ በትዊተር ገጻቸው "እየተደሰትንበት የነበረው የነጻነት ቀን በአጭሩ ተጨናግፏል። በኢላድ ሞትን ያስከተለው ድርጊት እጅግ አስደንግጦናል" ሲሉ አስፍረዋል።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው "ንጹሃንን ኢላማ ያደረገውን ይህንን ዘግናኝ ድርጊት" አሜሪካ አጥብቃ እንደምታወግዘው ትላንት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ይህ ጥቃት እንደ አውሮፓውያኑ ከ2006 በኋላ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እራኤል ውስጥ በፍልስጤማውያን እና የአረብ የዘር ሀረግ ባላቸው ሰዎች ጥቃት በተፈጸመ በሳምንታት ውስጥ ያጋጠመ ነው።

በዚህ ጥቃት የአርብ ዘር ሀረግ ያለው ፖሊስ እና 2 ዩክሬናውያንን ጨምሮ 16 እስራኤላውያን ተገድለዋል።

በአጻፋው እስራኤል በፍልስጤም ከተሞች በወሰደችው እርምጃ ነገሩን ሲመለከቱ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ 26 ሰዎች ሞተዋል።

እስራኤል ከነጻነት ቀኗ አንድ ቀን ቀደም ብላ በጦርነት እና በጥቃት ያጣቻቸውን ሰዎች ትዘክራለች።

እስራኤል በውሮፓውያኑ 1948 የተመሠረተች ሲሆን ይህ ቀን በዘመን አቆጣጠራቸው መሠረት በየዓመቱ ይከበራል።