ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋይት ሀውስ ጥቁር ሴት ቃል አቀባይ ተሾመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካሪን ጄን-ፒይር የመጀመሪያዋ ጥቁር፣ ሴት፣ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ቃል አቀባይ ሆና በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተሰይማለች።
የ44 ዓመቷ ካሪን ቦታውን የምትረከበው ከጄን ሳኪ ነው። ከቀጣዩ ሳምንት በኋላ ከዋይት ሀውስ ዘገባ ለሚሠሩ ጋዜጠኞች መረጃ መስጠት ትጀምራለች።
ጄን ሳኪ ግራ ዘመሙ ኤምኤስኤንቢሲ ውስጥ በቅርቡ ሥራ እንደምትጀምር ተገልጿል።
ቦታዋን የምትረከበውን ቃል አቀባይ "በሥነ ምግባር የታነጸች ድንቅ ሴት" ስትል ገልጻለች።
"የራሷ የአሠራር ስልት አላት። ድንቅና የላቀ ችሎታዋን እንደምታሳይ አልጠራጠርም" ስትለም አክላለች።
የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ የአሜሪካ መንግሥት ፊት ሆኖ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ለመላው ዓለምም ይታያል።
ማንኛውም ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም ብሔራዊ አደጋ ሲከሰት ቀድመው የሚታዮት እነዚህ ቃል አቀባዮች ናቸው።
ቃል አቀባዮች ፖሊሲ ባያረቁም አንድ የአሜሪካ አስተዳደር በሕዝቡ ዘንድ በምን መንገድ እንደሚታይ ይቀርጻሉ።
የባይደን አስተዳደር እስከ ዛሬ ድረስ በፖለቲካው መድረክ ገሸሽ የተደረጉ ጥቁር ሴቶችን በማሳተፍ ቀጥሏል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ካሚላ ሐሪስ፣ የአገር ውስጥ ፖሊሲ ካውንስል ቃል አቀባይ ሱዛን ራይስ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ኬታንጂ ብራውን ጃክሰን፣ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
ካሪን ጄን-ፒይር ከዚህ ቀደም በኤምኤስኤንቢሲ ተንታኝ ነበረች።
በፖለቲካው የሁለት አሥርታት ተሞክሮ አዳብራለች።
በፍሬንች ካረቢያኗ ማርቲኒኪው ደሴት ተወልዳ ኒው ዮርክ አድጋለች። በኦባማ አስተዳደር ቁልፍ ቦታ ከነበራቸው አንዷ ናት።
እአአ በ2016 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ ሙቭኦን የተባለው ብሔራዊ ንቅናቄ ቃል አቀባይ ነበረች።
ባይደን ካሚላ ሐሪስን ምክትላቸው አድርገው ከመረጡ በኋላ በቃል አቀባይነት ሠርታለች።
የፊታችን ጥቅምት በአሜሪካ የአስተዳደር አጋማሽ ምርጫ ይካሄዳል። ይህም ባይደን ፕሬዝዳንት ሆነው የሚቀጥሉበት ዓመታት በምን አቅጣጫ እንደሚጓዙ ይወስናል።












