በእየሩሳሌም አል-ዓቅሳ መስጊድ በተቀሰቀሰ ግጭት ከ150 በላይ ፍልስጤማውያን ቆሰሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
እየሩሳሌም በሚገኘው አል-ዓቅሳ መስጊድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከእስራኤል ፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት ከ150 በላይ ፍልስጤማውያን መቁሰላቸውን የፍልስጥኤም የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የእስራኤል ፖሊስ በበኩሉ መኮንኖቹ ወደ ስፍራው የገቡት በርችት፣ ድንጋይ እና በሌሎች ነገሮች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ነው ብሏል።
ሶስት የእስራኤል ፖሊሶች ተጎድተዋል ብሏል።
ስፍራው በእስልምና እምነት ተከታዮች እንዲሁም በአይሁዶች ዘንድ ደግሞ የታቦር ተራራ ተብሎ የሚጠራው ቅዱስ ስፍራ ሲሆን በሁለቱም እምነት ተከታዮች ዘንድ ታሪካዊ እንዲሁም እንደ ቅዱስ ስፍራ ይቆጠራል።
በእስራኤል እና ፍልስጥኤም ያለው ውጥረት በቅርብ ጊዜያት ተባብሶ ቀጥሏል።
ፍልስጥኤማውያን ባደረሱት ጥቃት እስራኤላውያን ሞተዋል የተባለ ሲሆን እስራኤም በቁጥጥሯ ስር ባለው ዌስት ባንክ ባደረገችው ከበባ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
በሰሜናዊ ዌስት ባንክ ጄኒን ግዛት እስራኤል ባደረገችው ጥቃት ሐሙስ ዕለት የቆሰለው የ17 ዓመቱ ፍልስጤማዊ አርብ ዕለት ህይወቱ ማለፉን የፍልስጥኤም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል በጄኒን ግዛት ባደረገችው ከበባም ከ20 የሚበልጡ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን በርካታዎቹም ታጣቂዎች ናቸው ተብሏል።
ይህም ባለፈው ሐሙስ አንድ ፍልስጤማዊ ሶስት እስራኤላውያን መግደሉን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ ጥቃት በእስራኤል አረቦችና በፍልስጤማውያን ዘንድ በእስራኤል ላይ የተፈጸመ አራተኛ ጥቃት መሆኑ ተነግሯል። በ
ዚህም 12 እስራኤላውያን እና ሁለት ዩክሬናውያን የተገደሉ ሲሆን ይህም በእስራኤል ውስጥ በ15 አመታት ውስጥ የደረሰ አስከፊ ጥቃት ነው ተብሏል።
የእስራኤል ፖሊስ እንዳስታወቀው በርካታ ፍልስጤማውያን አንዳንዶቹ የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድን ሃማስን ባንዲራ ይዘው በአገሬው አቆጣጠር ከቀኑ አስር ሰዓት ወደ መስጊዱ ገብተው ድንጋይ እና ርችት መወርወር ጀመሩ።
ፖሊስ እንደሚለው ብጥብጥ የፈጠሩትን ተቃዋሚዎች ለመበተን ወደ ስፍራው ከመግባቱ በፊት የአርብ ሰላትና ጸሎት እስኪጠናቀቅ እንደጠበቀ መቆየቱን ገልጿል።
ግለሰቦቹ ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩት ከመስጊዱ በታች ባለው ስፍራ የአይሁድ አምላኪዎች ወደነበሩበት ግቢ ነው ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሁከቱ ወቅት ፖሊሶች ወደ መስጊዱ ቅጥር ግቢ ገብተዋል በሚል በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተሰራጨውን ዘገባ አስተባብሏል።












