በናይጄሪያ ባቡር ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት በኋላ 168 ሰዎች የገቡበት አልታወቀም ተባለ

ታትሟል

ባለፈው ሳምንት በናይጄሪያ ባቡር ላይ የተከፈተውን ከባድ ጥቃት ተከትሎ ባቡር ውስጥ የነበሩ 168 ሰዎች እስካሁን ያሉበት አለመታወቁን የሀገሪቱ የባቡር አስተዳዳር ኩባንያ አስታወቀ።

የገቡበት አልታወቀም ከተባሉት 168 ሰዎች መካከል ምን ያህሉ በጥቃት አድራሾቹ እንደታገቱ ግልጽ አይደለም ተብሏል። አንዳንዶቹ ከጥቃቱ ተርፈው ለፖሊስ ሳያሳውቁ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

ትላንት ሰኞ ታጣቂዎች የሀገሪቱን ዋና ከተማ አቡጃ ከሰሜናዊቷ ካዱና ጋር የሚገናኘውን የባቡር መሰስመር ላይ ባደረሱት ጥቃት ፈንዳታ ደርሷል።

በዚህ ጥቃት ቢያንስ ስምንት ተሳፋሪዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

ይህ ጥቃት ካስከተለው አደጋ የተረፈ አንድ ሰው የባቡር ፉርጎ የመቀየር ውሳኔው የሱን እና የቤተሰቡን ህይወት እንዴት እንደተደገው ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በህይወት በመኖሬ እና ደህና በመሆኔ ደስተኛ ነኝ" ያለው ከአደጋው የተረፈው ግለሰብ "ለተገደሉት እና ለተጎዱት በጣም አዝኛለሁ። አደጋው እኔ ላይም ሊከሰት ይችል ነበር" ብሏል።

ሰውዬው ባቡሩ ሊያመልጠው የነበረ ሲሆን ከባለቤቱ እና ከሁለት ልጆቹ ጋር ተሯሩጦ እንደደረሰበት ተናግሯል።

ባበቡር ውስጥ ከገባ በኋላ አብረውት የነበሩት ተሳፋሪዎች የተሳሳተ መቀመጫዎች ላይ እንዳለ ነገሩት። በዚህም ምክንያት ቤተሰቡን ይዞ ከነበረበት ፉርጎ ወደ ሌላኛው ተዘዋወረ።

ተቀምጠውበት የነነበረው ፍርጎ 17 ቁጥር ሲሆን ታጣቂዎች አደጋ ያደረሱበት ነው። ይህ 'እድለኛ' ሰው ግን ከዚህ ወጥቶ ምንም አደጋ ወዳላጋጠው ፉርጎ 12 ተዘዋውሯል።

አደጋው በደረሰበት ሰዓት ከፈተኛ ድምጽ መስማቱን እና ባቡሩንም እንዳናጋው የሚናረው ይህ ሰው ታጣቂዎቹ ባቡሩን ከበውት በሚመስል መልኩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ድንገተኛ የተኩስ ድምፅ እንደነበረ አስረድቷል።

"ሌሎች ተሳፋሪዎች ሲያደርጉ ተመልክተናል ከቤተሰቦቼ ጋር በባቡሩ ወለል ላይ በደረታችን ተኛን" ሲል ገልጿል።

"ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ታጣቂዎቹ ወደ ፍርጎዎቹ የገቡበት ምክንያት ሌሎች ፍርጎዎች ውስጥ ተሳፋሪዎች ላይ ትእዛዝ እየሰጡ ሲጮሁ የሚመስል ሁኔታ ሰምቻለሁ። በፍርጎዎቹ ውስጥም የተኩስ ድምጽ ነበር። ሰዎች ከፍርጎው ወጥተው ወደ ጫካ እንደኤገቡ ትእዛዝ ሲሰጡ ነበር። እኛ ወደ ነበርንበት ፍርጎ ማንም አልገባም" ሲል ተናግሯል። ፍርጎ ለመቀየር ያደረኩት ውሳኔ የኔ እና የቤተሰቤን ህይወት ታድጓል" ብሏል።

ለዚህ የባቡር ጥቃት የትኛውም ቡድን ሃላፊነት አልወሰደም። ሆኖም የካዱና ግዛት ገዥ የቦኮ ሃራም እስላማዊ ታጣቂዎች ከሌላ አፋኝ ቡድን ጋር በመተባበር ያደረጉት ሊሆን እንደሚችል ገልጸው የነፍስ አድን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በባቡሩ የተሳፈሩ 362 መንገደኞች የተመዘገቡ ሲሆን የናይጄሪያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የገቡበት ያልታወቀው 168 ሰዎች ሁሉም ተሳፋሪዎች ወይም የባቡሩ ሰራተኞች እንዳሉበት አልገለጸም። ባቡሩ ላይ 970 ተሳፋሪዎች እንደነበሩ በመጀመሪያ የተመዘገበ ሲሆን ይህ የቁጥር ልዩነት እንዴት እንደመጣ አልታወቀም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ደግሞ ዘመዶቻቸው ከጠፉባቸው መካከል አጋቾቹ ደውለው በእነሱ እጅ እንደሚገኙ ነግረዋቸዋል።

በሰሜን ምእራብ ናይጄሪያ እንዲህ አይነት የወንበዴ ቡድኖች መበራከታቸው የሚነገር ሲሆን የካዱና ግዛት ማዕከላቸው እንደሆነች ይቆራል። በዚህ ወር መግቢያ የካዱና አየር ማረፊያ ጥቃት እንደደረሰበት የሚያመላክቱ ዘገባዎች ወጥተዋል።

ባለፉት 24 ወራት ውስጥ ብቻ በናይጄሪያ የታጠቁ ቡድኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለው በሺዎች የሚቆጠሩ ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርገዋል።