በሃርጌሳ የገበያ ሥፍራ በደረሰው የእሳት አደጋ በቢሊየን ዶላር የሚገመት ውድመት ደርሷል ተባለ

የሶማሌላንድ ዋና ከተማ በሆነችው ሃርጌሳ የደረሰው ከፍተኛ የእሳት አደጋ
ታትሟል

ባለፈው አርብ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሃርጌሳ በገበያ ስፍራ በተከሰተ የእሳት አደጋ በቢሊየን ዶላር የሚገመት ንብረት ሳይወድም እንዳልቀረ ተገለጸ።

በአደጋው ለተጎዱት ከአጎራባች አገራት ዕርዳታ መግባት መጀመሩን ተከትሎ በአካባቢው አስተዳደር የተቋቋመው ኮሚሽን፣ የእሳት አደጋው ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመቱ ንብረቶችን ሳያወድም እንዳልቀረ አስታውቋል።

በእሳት አደጋው ምክንያት ከደረሰው ከፍተኛ ውድመት በኋላ የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጋርተዋል።

አርብ አመሻሽ ላይ የተነሳው እሳት በአጠቃላይ የገበያውን ሥፍራ አውድሞታል። በሃርጌሳ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን ሜዳ ላይ ያስቀረውን ይህንን እሳት ለማጥፋትም ሰዓታት ፈጅቷል።

በሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ የተዋቀረውና በአደጋው የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራው ኮሚሽን በአደጋው ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ውድመት ሳይደርስ እንዳልቀረ አመልክቷል።

"እንደ የመጀመሪያ ደረጃው ሪፖርት ከሆነ በእሳት አደጋው የደረሰው የጉዳት መጠን ከ1.5 እስከ 2 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል" ሲሉ የሃርጌሳ ከተማ ከንቲባ አብዲካሪን አሕመድ ሞጌ ተናግረዋል።

የገበያ ሥፍራው ከአደጋው በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Fahad Karie

የምስሉ መግለጫ, የገበያ ሥፍራው 2 ሺህ የሚሆኑ ሱቆችንና ሸዶችን የያዘ ነበር

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሁሴን ሮብሌ እሁድ ዕለት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ከተወያዩ በኋላ ባደረጉት ንግግር መንግሥታቸው በሃርጌሳ የንግድ ገበያ ዋሂን ለደረሰው ከባድ የእሳት አደጋ ለአደጋ ጊዜ ምላሽ የሚውል 11.7 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን እና የአሜሪካ የኮንግረንስ አባል ኢልሃን ኦማርን ጨምሮ የዓለም መሪዎች በሃርጌሳ ሕዝቦች ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን የገለፁ ሲሆን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከጎናቸው እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

የገበያው ሥፍራ በመቶዎች በሚቆጠሩ ትናንሽ ሱቆች እና ነጋዴዎች የተጨናነቀ ነበር።

በዚህ በሃርጌሳ ከተማ የንግድ ማዕከል በሆነውና በሺዎች የሚቆጠሩ ሹቆችና ሸዶች መገኛ ዋሂን የገበያ ሥፍራ ላይ የደረሰው የእሳት አደጋ መንስኤ እስካሁን አልታወቀም።

የገበያ ሥፍራው ለኢትዮጵያ፣ ለጂቡቲ እና ለተወሰኑ የሶማሊያ አካባቢዎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ ሦስተኛው ትልቁ የገበያ ሥፍራ ነበር።

በአደጋው ለተጎዱት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ ሲሆን ጎረቤት አገራትም የልዑካን ቡድን ወደ ሶማሊላንድ በመላክ ከሃርጌሳ ሕዝብ ጋር የደረሰውን ጉዳት መጋራት ችለዋል።

ሶማሊላንድ እአአ በ1991 የሲያድ ባሬ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ከሶማሊያ ነጻ መውጣቷን ያወጀችው ከ30 ዓመታት በፊት ሲሆን እስካሁን ግን ይፋዊ እውቅና አላገኘችም።