'ልጃችሁ አርፋለች' ከልክ ያለፉ 'የኤፕሪል ዘ ፉል' ቀልዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንጆቹ ወርሃ ኤፕሪል የመጀመሪያ ቀን ኤፕሪል ፉልስ የተባለው የዳቦ ስም አለው። በዚህ ቀን ሰዎች ይዋሻሉ፣ 'ፕራንክ' ይደራረጋሉ፣ ሲሸዋወዱ ይውላሉ።
በስኳር እቃ ውስጥ ጨው ቀይሮ ማታለል አንዱ የተለመደ የኤፕሪል ዘ ፉል ቀን ስልት ነው።
አንዳንዴ በኤፕሪል ዘ ፉል ቀን የሚነገሩ ቀልዶች ከልክ ያለፉ ይሆኑና ፈገግታ ከመጫር ይልቅ ሀዘን እና ጉዳት የሚያስከትሉ ይሆናሉ።
ጥላሁን ግርማ ከኤፕሪል ዘ ፉል ቀን ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ሲናገር በብስጭት ነው። ጥላሁን ይህን በተመለከተ በፌስቡክ ገጹ ያጋራውን ታሪክ እንዲነግረን ጠየቅነው። የሆነውንም እንዲህ ሲል አስታውሶታል።
ክስተቱ ያጋጠመው ከዓመታት በፊት ቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ ሳለ ነበር። ቁርቁር ተብሎ በሚጠራ ስፍራ።
ጥላሁን በአከራዩ ግብዣ አንድ ድግስ ላይ ይገኛል። ይህ ግብዣ ‘ምስጋና’ ለማቅረብ የተዘጋጀው ነው። ልጃቸው ከሞት በመትረፏ ምስገና ለማቅረብ የተዘጋጀ ድግስ።
በአዲስ አበባ የኮሌጅ ተማሪ የሆነች ልጅ ያላችው ቤተሰብ ቤት ስልክ ይጠራል። መደበኛው ባለገመዱ የቤት ስልክ። ዘመኑ እንደ ዛሬ ሞባይል ስልክ የበዛበት አልነበረም።
በዛኛው ጫፋ ያለው ድምጽ፤ “ልጃችሁ በደረሰባት የመኪና አደጋ ሞታለች። ሬሳዋን ሚኒሊክ ሆስፖታል ሄዳችሁ ውሰዱ” አለ።
በቤቱ ከፍተኛ ለቅሶ እና ሃዘን ሆነ። የልጅቱ እናት ከፍተኛ ሐዘን ላይ ወደቁ።
የአካባቢው ሰዎች እና ቤተሰብ አስክሬን ለማምጣት ሚኒሊክ ሆስፒታል ተገኙ። የልጅቱ አስክሬን ግን ሊገኝ አልቻለም። ይህ በቤተሰብ ላይ ዳግም ሌላ መሪር ሐዘን ፈጠረ።
ሕይወቷ አልፏል የተባለችው የኮሌጅ ተማሪ፤ እርሷ ቤተሰብ ጋር ስልክ ካልደወለች እርሷን በስልክ ማግኘት ቀላል ያልሆነበት ዘመን ነበር።
በቀጣዩ ቀን የቤተሰብ አባላት ወጣቷ ወደምትማርበት ኮሌጅ ይሄዳሉ። ሞታለች የተባለችው ልጅ ወደ መማሪያ ክፍል ልትገባ ስትል ይመለከቷታል።
በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈው ቤተሰብ፤ የልጃቸው ሞት ተደውሎ የተነገረው በኤፕሪል 1 ቀን መሆኑን ሲገነዘብ ከልክ ያለፉ 'የኤፕሪል ዘ ፉል' ቀልድ መሆኑን ይረዳዋል።
ዛሬም ድረስ ያን የስልክ ጥሪ ማን እንዳደረገ ቤተሰቡ አያውቅም።
“ሁሉም ነገር ልክ ሊኖረው ይገባል”
ይህን ታሪክ ያጋራን ጥላሁን፤ ይህ በኛ ባህል ውስጥ የሌለ ነው ይላል።
“ከነጮች መውሰድ ያለብንን ትተን የማይሆነውን ነው እየወሰድን ያለነው” በማለት ይህ ቀን ሰዎችን ፈገገ ከማሰኘት ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ያስረዳል።
የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ “ከሥራ ተባረርኩ” ብሎኝ ገንዘብ እንደቸገረው በነገረኝ ጊዜ በጣም ተጨንቄ ነበር። “ሙሉ ቀን ስጨነቅ ውዬ ገንዘብ ላስገባለት ሲሄድ ጓደኞቹ ሳቁብኝ” ይላል ጥላሁን።
“ይሄ ሰው ከአሁን በኋላ ምንም ነገር ቢለኝ ላምነው አልችልም፤ አንዴት ላምነው እችላለሁ?” በማለት ይጠይቃል።
የቢቢሲ ፓናሮማ ኤፕሪል ዘ ፉል ዘገባ
በመላው ዓለም በኤፕሪል 1 ቀን ሰዎችን ለማሞኘት ከተነገሩ ሐሰተኛ ዘገባዎች መካከል ቢቢሲ እአአ 1957 ላይ የፓስታ እጥረትን በተመለከተ የሥራው ዘገባ ነበር።
በጊዜ በከባድ የክረምት ወቅት ምክንያት የፓስታ እጥረት አጋጥሞ ነበር። ታዲያ ይህ ዘገባ የስዊዘርላንድ ገበሬዎች የፓስታ እጥረቱን የሚቀርፍ ምርት ለገበያ እያቀረቡ ነው ይላል።
ፓኖራማ በዚህ የቴሌቪዥን ዘገባው፤ ገበሬዎች ከዛፍ ላይ ፓስታ ሲቀነጥሱ አስመለከተ።
በርካታ ተመልካቾች ይህ ዘገባ እውነት መስሏቸው ነበር። ብዙዎች ውደ ቢቢሲ ስቱዲዮ በመደወል ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ እያሉ ሲጠይቁ ነበር።












