ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የፑቲን አማካሪዎች በጣም ስለሚፈሯቸውን እውነቱን ለፕሬዝደንቱ አይናገሩም አለች
ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት አማካሪዎቻቸው እውነቱን አይነግሯቸውም ስትል አሜሪካ ለሰነዘረችው ትችት ሩሲያ በበኩሏ ምዕራባውያን ሩሲያ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አያውቁም ስትል ምላሽ ሰጠች።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዋይት ሐውስ እንደሚለው ከሆነ የፑቲን አማካሪዎች ፕሬዝደንቱን ስለሚፈሩ በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ጉዳት ምን ያህል አገሪቱን እየጎዳ እንዳለ በግልጽ አይናገሩም።
የዩናትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት ደግሞ በዩክሬን እየተዋጉ ያሉት የሩሲያ ወታደሮች ሞራል ላሽቋል፣ አቅርቦት ቀንሷል፣ ወታደሮችም ትዕዛዝ አንቀበልም እያሉ ነው ብሏል።
ሞስኮ በበኩሏ ምዕራባውያን ስለ ሩሲያ የሚናገሩትን አያውቁም ትላለች።
የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ "ምዕራባውያን በክሬምሊን ምን እየተካሄደ እንደሆነ አይረዱም፤ ፕሬዝደንት ፑቲንን አይረዱም፤ ውሳኔዎች እንዴት እንደሚወሰኑ አይገባቸውም፤ የሥራ ዘዴያችንን አይረዱም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ፑቲን "የሩሲያ ጦር እንዳሳሳታቸው ተሰምቷቸዋል" የሚል መረጃ አሜሪካ እንዳላት እና ይህም፤ "በፑቲን እና በሩሲያ ጦር አመራሮች መካከል ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል" ብለው ነበር።
ምዕራባውያኑ ሩሲያ ከቀናት በፊት በዩክሬን መዲና ኪዬቭ አቅራቢያ የማካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻዎቼን እቀንሳለሁ ማለቷ የዚሁ ውጤት ነው ይላሉ።
የዩኬ የሳይበር ጥቃት ደኅንነት ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት ጄሬሚ ፍሌሚንግ፤ ሩሲያ የጦር ዘመቻዋን ለመቀነስ ማሰቧ ቀድማ አንስተኛ ግምት ሰጥት እንደነበረ እና ዳግም ማሰብ እንዳለባት የሚያሳይ ነው ይላሉ።
"የሩሲያ ወታደሮች መሳሪያ እና ሞራል አጥሯቸው፤ ትዕዛዝ አንቀበልም ሲሉ ተመልክተናል። የራሳቸውን አውሮፕላን በስህተት መትተው ሲጥሉ ሁሉ ተስተውሏል" ሲሉ ፍሌሚንግ በአውስትራሊያ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ንግግር አድርገዋል።
"ምንም እንኳ የፑቲን አማካሪዎች እየሆነ ስላለው ነገር መናገር ቢፈሩም (ለፑቲን) የሩሲያ መንግሥት ሁኔታውን እንዴት አቅልሎ እንዳየው ግልጽ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ሩሲያ ጦሯን ከኪዬቭ ርቆ ባለ ቦታ ዳግም እያደራጀች ነው ይላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፈረንሳይ መንግሥት የአገሪቱ ጦር ደኅንነት ኃላፊ ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር እንደምትችል ቀድሞ መገመት አልቻሉም በሚል ከሥራ ማሰናበቱ ተዘግቧል።
በሌላ ዜና በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው የዩክሬን ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ማሪዩፖል ሩሲያ ለአንድ ቀን የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሃሳብ አቅርባለች።
ሩሲያ ይህን ያለችው ፕሬዝዳንት ፑቲን በከተማዋ ላይ የሚደርሰው ጥቃት የሚቆመው ማሪዩፖል በሩሲያ ቁጥጥር ስትገባ ነው ካሉ በኋላ ነው።
በዚህ ጦርነት እስካሁን ድረስ ከአጠቃላይ የዩክሬን ዜጎች ሩብ ያክሉ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፤ አራት ሚሊዮን የሚሆ ዩክሬናውያን ደግሞ ከአገር ውጭ ተሰደዋል።