ሩሲያ በወር 5ሺህ ዶላር የሚከፈላቸው ተዋጊዎችን ሶሪያ ውስጥ እየመለመለች ነው ተባለ

የሶሪያ ወታደሮች የፕሬዝዳንት ፑቲንን ፎቶ ይዘው
የምስሉ መግለጫ, የሶሪያ ወታደሮች የፕሬዝዳንት ፑቲንን ፎቶ ይዘው
ታትሟል

ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ በምታካሂደው ጦርነት ከሠራዊቷ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ ፈቃደኛ ተዋጊዎችን በከፍተኛ ከፍያ ሶሪያ ውስጥ እየመለመለች መሆኗ ተነገረ።

ከአንድ ወር በላይ በሆነው ጦርነት ውስጥ ከዩክሬን ኃይሎች በኩል ከባድ መከላከል የገጠማት ሩሲያ ፈቃደኛ የሆኑ የወዳጇ የሶሪያ ዜጎችን ለጦርነቱ እየመለመለች መሆኗን ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።

በዚህም ዩክሬን ውስጥ ለሩሲያ ለመዋጋት የሚሹ ብቁ ለሆኑ ሶሪያውያን በወር ከ5,000 ዶላር በላይ እንደምትከፍል ተነግሯል።

አንድ ከሩሲያ ወገን ለመሰለፍ ፈቃደኛ የሆነ የሶሪያ ወታደር እንዳለው፣ ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ጭፍጨፋ እየፈጸመች መሆኑን እንደሚያምን፣ ነገር ግን "የሚበሉትን ያጡ ሶሪያውያን ድሆችን ደግሞ እየረዳች ነው" ብሏል።

ወታደሩ ጨምሮም ለሩሲያ ለመዋጋት ፈቃደኛ የሆነው የሚከፈለው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ገልጾ፣ ቤተሰቦቹ ግን ወደ ጦር ግንባር እንዳይሄድ ቢፈልጉም የሚገኘውን ገንዘብ በማሰብ መወሰኑን ተናግሯል።

ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ለምታካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ከሶሪያ ለምትመለምላቸው ፈቃደኛ ተዋጊዎች በየወሩ ከምትከፍለው ከፍተኛ ገንዘብ በተጨማሪ ወታደሮቹ በጦርነቱ ላይ ቢገደሉ 50ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያህል ለቤተሰቦቻቸው ይከፈላል ተብሏል።

በዚህም መሠረት አስካሁን ድረስም ቢያንስ 200 ሶሪያውያን ዩክሬን ውስጥ ከሩሲያ ጎን ሆነው ለመዋጋት ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል።

የዩክሬን መንግሥትና የሶሪያ ዋነኛ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ፈቃደኛ ተዋጊዎችን ለሩሲያ ለመመልመል 14 ማዕከላት በተለያዩ የሶሪያ ክፍሎች ውስጥ ተቋቁመዋል።

ከአስር ዓመት በፊት በአብዛኛው የአገሪቱ ከፍሎች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችው የሶሪያ መንግሥት ከሩሲያ ከፍተኛ ወታደራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ ሲያገኝ ቆይቷል።

ምዕራባውያን የተለያዩ አማጺያንን በመርዳት ከሥልጣናቸው ሊያስወግዷቸው የተነሱባቸው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድን የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ባደረጉላቸው ወታደራዊ ድጋፍ አማጺያኑን በመቋቋም በሥልጣናቸው ላይ ቆይተዋል።

በሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት የሩሲያ ከፍተኛ የጦር መሪዎች፣ አማካሪዎች እና የአየር ኃይሉ ተሳታፊ በመሆን የሶሪያ ሠራዊት እንዲጠናከር አግዘዋል።

አሁን ደግሞ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ወረራ ተከትሎ የገጠማትን የምዕራባውያንን ጫናና ከባድ ወታደራዊ መከላከል ለመቋቋም አጓጊ ክፍያ በመስጠት ከወዳጇ ሶሪያ ፈቃደኛ ተዋጊዎችን እየመለመለች መሆኑን ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው።

በተመሳሳይ ዩክሬንም ከሩሲያ ጋር ለምታደርገው ጦርነት ከጎኗ ሆነው ለመዋጋት ለሚፈልጉ የተለያዩ አገራት ዜጎች ጥሪ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን፣ ነገር ግን ስለክፍያ የተባለ ነገር የለም።