ሴኔጋል ግብፅን በመርታት ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ አለፈች

ሳዲዮ ማኔ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ሴኔጋል ግብጽን በማሸነፍ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋገጠች።

በመለያ ምት አላፊው በተለየበት ይህ ጨዋታ የሊቨርፑሉ ሳዲዮ ማኔ ማሸነፊያዋን የፍጹም ቅጣት ምት በመምታት ግብጽን በሚወክለውና በክለብ ደረጃ አብሮት የሚጫወተው ሞሀመድ ሳላህን ከዓለም ዋንጫ ውጪ ማድረግ ችሏል።

ግብጽ ውስጥ በተካሄደው በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ግብጽ አንድ ለባዶ አሸንፋ የነበረ ቢሆንም በሴኔጋሉ የመልስ ጨዋታ ደግሞ በተራዋ ሴኔጋል አንድ ለባዶ አሸንፋለች። በዚህም በአጠቃላይ ውጤቱ አቻ ሆኗል።

አገራቱ በመለያ ምት ከተለያዩ በኋላ ሴኔጋሎች ደስታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲጨፍሩ በተቃራኒው ሞሀመድ ሳላህ እና ግብጻውያን ግን የሆነውን ማመን ከብዷቸውና አንገታቸውን ደፍተው ታይተዋል።

50 ሺ ተመልካቾችን መያዝ በሚችለው ስቴዲየም በተደረገው የሴኔጋሉ ጨዋታ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ተጨማሪ ሰአት ቢያመራም ምንም ግብ አለመቆጠሩን ተከትሎ ወደ አስጨናቂው የመለያ ምት ሄደዋል።

ሴኔጋል አንድ ለባዶ እንድታሸንፍ ግቧን ያስቆጠረው ቡላዬ ዲያ ሲሆን ጨዋታው በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ላይ ነው አገሩን መሪ ማድረግ የቻለው።

በመለያ ምቱ ሞሀመድ የቡድኑ አምበል ሳላህን ጨምሮ አራት የግብጽ ተጫዋቾች ኳሷን ከመረብ ጋር ማገናኘት የቃታቸው ሲሆን የመጨረሻዋንና ሴኔጋልን አሸናፊ ያደረገችውን መለያ ምት ወደ ግብነት የቀየረው ደግሞ የሊቨርፑሉ ሳዲዮ ማኔ ነው።

በሌሎች የአፍሪካ ምድብ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ጋና፣ ቱኒዚያ፣ ካሜሩን እና ሞሮኮ ወደ ኳታር መሄዳቸውን አረጋግጠዋል።

ጋና በመጀመሪያው ዙር በሜዳዋ ከናይጄሪያ ባደረገችው ጨዋታ ጨዋታ ዜሮ ለዜሮ ነበር ያጠናቀቀችው። ናይጄሪያ የካሄደው የመልሱ ጨዋታ ደግሞ አንድ መጠናቀቁን ተከትሎ ጋና ከሜዳ ውጪ ባገባ በሚለው ለኳታር የዓለም ዋንጫ ማለፏን አተጋግጣለች።

ካሜሩን ደግሞ አልጄሪያን በማሸነፈው ለስምንተኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫው ማለፍ ችላለች። ምንም እንኳን በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አልጄሪያ አንድ ለባዶ ብታሸንፍም በመልሱ ጨዋታ ግን ካሜሩን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ደጋፊዎቿን ጮቤ አስረግጣለች።

በሌላ በኩል ቱኒዚያ በመጀመሪያው ዙር ከማሊ ያደረገችው ጨዋታ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቀችው። ነገር ግን ቱኒስ በተካሄደው የመልስ ጨዋታ አንድ ለባዶ በማሸነፍ ወደ ኳታር የሚጓዙት አምስቱን የአፍሪካ አገራት ተቀላቅላለች።

ሞሮረኮ ደግሞ ከሌሎቹ የአፍሪካ ምድብ ጨዋታዎች አንጻር ቀለል ያለ ፈተና ነበር የገጠማት። በመጀመሪያው ዙር ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ያደረገችውን ጨዋታ አንድ አቻ ብታጠናቅቅም በሜዳዋ ባደረገችው የመልስ ጨዋታ ግን 4 ለ1 በማሸነፍ ወደ ኳታር መሄዷን አረጋግጣለች።

በአውሮፓ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች ደግሞ በርክስቲያኖ ሮናልዶ የምትመራው ፖርቹጋል እና የሌዋንዶውስኪ አገር ፖላንድ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

ፖርቹጋል ለማንቸስተር ዩናይትድ በሚጫወተው ብሩኖ ፈርናንዴዝ ሁለት ግቦች ሰሜን ሜሴዶኒያን ያሸነፈች ሲሆን ፖላንድ ደግሞ ሌዋንዶውስኪ እና ዜሌንስኪ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ስዊድንን በማሸነፍ ወደ ኳታር ጎዟቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሳዲዮ ማኔ ለተከታታይ ዓመታት ዕጩ የሆነበትን ሽልማት ዘንድሮ ያሳካው ይሆን?