ባይደን "ፑቲን ሥልጣን ላይ መቆየት የለበትም" ማለታቸው እያወዛገበ ነው

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በፖላንድ መዲና ዋርሶው ውስጥ ስለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያደረጉት ንግግር አወዛጋቢ ሆኗል።

ባይደን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ስለፈጸመችው ወረራና ስለፕሬዝዳንት ፑቲን ንግግር ባደረጉበት ጊዜ "ኧረ በፈጣሪ፣ ይህ ሰው ሥልጣን ላይ መቆየት የለበትም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ በሩሲያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ፍላጎትና አላማ እንዳላት የሚያመለክት ነው በሚል፣ በሁለቱ ኃያል አገራት መካከል ያለውን ፍጥጫ ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ነገር ግን ፕሬዝዳንት ባይደን በዋርሶው ንግግር ካደረጉ በኋላ ዋይት ሐውስ ስለ ንግግራቸው ይዘት ማብራሪያ ለመስጠት ጊዜ አላጠፋም።

የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ከባይደን ንግግር በኋላ በፍጥነት "ባይደን የተናገሩት ሥልጣን ላይ ያለውን ሰው ስለመለወጥ አይደለም" ሲል ማስተባበያ አውጥቷል።

"ይህ ሰው ሥልጣን ላይ መቆየት የለበትም" የሚለው ንግግር በሩሲያ የመሪ ለውጥ እንዲኖር አሜሪካ ትፈልጋለች ተብሎ እንዳይተረጎም መግለጫው ይጠቁማል።

ሲያብራራም "ባይደን የተናገሩት ስለ መሪ ለውጥ አይደለም። የንግግራቸው ትኩረት ፑቲን በጎረቤት አገራት ላይ ሥልጣኑን ያለ አግባብ እንዳይጠቀም የሚያሳስብ ነው" ይላል የዋይት ሐውስ መግለጫ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ በሩሲያም ሆነ በሌላ አገር የመንግሥት ለውጥ የማድረግ ምንም አይነት እቅድ የላትም ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ፖላንድ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት እያነበቡ ካቀረቡት ንግግር ማብቂያ ላይ እንዲሁ በቃላቸው ፕሬዝዳንት ፑቲንን በሚመለከት ጣል ያደረጉት ንግግር ቁጣን ቀስቅሷል።

ብሊንከን ቁጣውን ለማብረድ በሰጡት ምላሽ ፕሬዝዳንቱ ለማለት የፈለጉት ፑቲን በዩክሬን ላይ ጦርነት እንዲያካሂዱ መፈቀድ የለበትም ነው ሲሊ አስተባብለዋል።

የሩሲያ መንግሥትም ለባይደን ንግግር በሰጠው ምላሽ፣ የራሳቸውን መሪ የመምረጥ መብት ያላቸው ሩሲያውያን ብቻ ናቸው በማለት ቁጣውን ገልጿል።

ብሊንከን ዛሬ አስራኤል ውስጥ እያደረጉት ባለው ጉብኝት "ፕሬዝዳንቱም ሆኑ ጽህፈት ቤታቸው ያሉት ገልጽ ነው። ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬንም ላይ ሆነ በሌላ አገር ላይ ወረራም ሆነ ጦርነት ሲከፍቱ ያሻቸውን ያድርጉ ሊባሉ አይገባም ነው ያሉት" ብለዋል።.

"በተደጋጋሚ ስንል እንደሰማችሁትና እንደምታውቁት፣ በሩሲያም ሆነ በሌላ ቦታ የሥርዓት ለውጥ የማምጣት እቅድ የለንም። በዚህ ጉዳይ ላይ የመወሰን መብት ያለው የየአገራቱ ሕዝብ፣ እንዲሁም ሩሲያውያን ናቸው" ሲሉ ብሊንከን አክለዋል።

ከባይደን ንግግር የዋይት ሐውስ መግለጫ በኋላ የወጣው ማብራሪያ በቀጣይ ከፑቲን ጋር ውይይት ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዳይፈጥር በሚል የወጣ መግለጫ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።

በተለይም ፑቲን የኒውክሌር ባለቤት የሆነች አገርን የሚመሩ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከዚህ በኋላ የንግግር በሮች ዝግ እንዳይሆኑ ለማድረግም ነው ዋይት ሐውስ ስለ ባይደን ንግግር ማብራሪያ የሰጠው።

የባይደን ንግግር "መሪ እንዲለወጥ ፈልገው ነው" በሚል ከተተረጎመ አለመረጋጋት እና ለመገመት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል።

ባይደን ንግግሩን ያደረጉበት የፖላንድ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ሉካሳዝ ጃስቲና ለቢቢሲ "የዓለማችን ኃያል አገር መሪ ዋርሶው መጥተው ስለ ወራሪዋ ሩሲያ በግልጽ ተናግረዋል" ብለዋል።

ቃል አቀባይዋ ጨምረውም "ምንጊዜም አምባገነን መሪን መለወጥ እንደሚቻል ባይደን ለሩሲያውያን ተናግረዋል። ስሜት የሚኮረኩር ንግግር ነው። ፑቲን በማኅበረሰባችን ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ጆሮ ሊሰጠው፣ ሊታመንም አይገባም" ሲሉ ተናግረዋል።

የባይደንን አወዛጋቢ ንግግር ያስተናገደችው ፖላንድ ከዩክሬን ጋር ድንበር ትጋራለች።

የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ከዩክሬን በመቀበል ትብብር አድርጋለች።

ወደ ፖላንድ ከገቡ ስደተኞች መካከል ዩክሬን ውስት ትምህርት ይከታተሉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል።