ሳላህ ወይስ ማኔ? ሮናልዶ ወይስ ጆርጂኒዮ? ማን ተሰናባች፣ ማንስ የዓለም ዋናጫ ተሳታፊ ይሆን?

Salah Mane

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ኳታር ከ8 ወራት በኋላ እንግዶቿን ተቀብላ ደማቁን የእግር ኳስ መድረክ ለማካሄድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ትገኛለች።

የአውሮፓ እና የአፍሪካ አገራትም በዚህ ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ ዛሬ እና ነገ ግጥሚያዎችን ያደርጋሉ።

የአፍሪካ ብርቅዬ ልጆች ሳዲዮ ማኔ እና ሞሐመድ ሳላህ ፊት ለፊት ተፋጠዋል። ከ11 ምርጥ የአውሮፓ አገራት ቡድኖች ወደ ኳታር ማቅናት የሚችሉት 3ቱ ብቻ ናቸው።

የአፍሪካ አገራት ተፋላሚዎች

አስር የአፍሪካ አገራት በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ፍልሚያ ያደርጋሉ።

ከእነዚህ መካከል ትልቅ ትኩረትን መሳብ የቻለው የሊቨርፑሎቹ ሞሐመድ ሳላህ እና ሳዲዮ ማኔን ያፋጠጠው የግብጽና ሴኔጋል ጨዋታ ነው።

ሁለቱን የሊቨርፑል ኮከቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ነገ ምሽት 4፡30 ይካሄዳል።

በካሜሩን አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ግብጽና ሴኔጋል ተገናኝተው ሴኔጋል ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ምንም እንኳን ሁለቱ ተጫዋቾች በክለብ ደረጃ ጥሩ የቡድን አጋሮች ቢሆኑም በብሔራዊ ቡድን ውድድሮች ግን በተቃራኒው ናቸው።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት የቻለው ማኔ ለአገሩ ትልቅ ነገር ማበርከት የቻለ ሲሆን ሞሐመድ ሳላህ ግን እስካሁን ከግብጽ ብሔራዊ ቡድን ጋር ዋንጫ ማንሳት አልቻለም።

በሌላ ፍልሚያ ደግሞ የምዕራብ አፍሪካዎቹ ጋና እና ናይጄሪያ ተፋጠዋል።

ሁለቱ አገራት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሲገናኙ ከ11 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያቸው ሲሆን ማን ወደ ኳታር ይሄዳል የሚለው በጣም አጓጊ ሆኗል።

በሌሎች ጨዋታዎች ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሞሮኮ፣ ማሊ ከቱኒዚያ እንዲሁም ካሜሩን ከአልጄሪያ ይገናኛሉ።

ሁሉም የመጀመሪያ ዙር የአፍሪካ ጨዋታዎች አርብ ዕለት መጋቢት 16/2014 የሚካሄዱ ሲሆን የመልስ ጨዋታው ደግሞ በሳምንቱ መጋቢት 20/2014 ይካሄዳል።

የአውሮፓ አገራት ተፋላሚዎች

አስር የአውሮፓ አገራት በ2022ቱ የኳታር የዓለም ዋንጫ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል። የአውሮፓ አገራት ሦስት ኮታ ይቀራቸዋል።

ሦስቱን ቦታዎች ለመያዝ የሚፋለሙት ደግሞ 11 አገራት ናቸው። ከእነዚህም መካከል የክርስቲያኖ ሮናልዶ ፖርቹጋል፣ የባየርን ሙኒኩ ሉዋንዶውስኪ ፖላንድ፣ ጣልያን፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ስዊድን ይገኙበታል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ የአገራቱ እርስ በርስ ፍልሚያ አንዳንድ ለውጦችን አስተናግዷል።

ሩሲያ ፖላንድን ትገጥም የነበረ ሲሆን ወረራውን ተከትሎ ፖላንድ በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር እንድታልፍ ተደርጓል።

ዩክሬን ከስኮትላንድ ጋር ልታደርገው የነበረው ጨዋታ ደግሞ እስከ ሰኔ ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል።

11 አገራት በሦስት ምድቦች የተደለደሉ ሲሆን ከእያንዳንዱ ምድብ አንድ አገር ብቻ ለኳታር የዓለም ዋንጫ ያልፋል።

ኦስትሪያ ከአውሮፓውያኑ 1998 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ትግል እየደረገች ሲሆን በምድቡ ከዌልስ ጋር ትጫወታለች።

ስኮትላንድም ብትሆን ልክ እንደ ኦስትሪያ ከ24 ዓመታት በኋላ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ እየታተረች ነው።

የሩሲያን ከውድድሩ መታገድ ተከትሎ ወደ መጨረሻው ዙር በቀጥታ ማለፍ የቻለችው ፖላንድ ከስዊድን አልያም ከቼክ ሪፐብሊክ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

በባየርን ሙኒኩ አጥቂ ሮበርት ሉዋንዶውስኪ የምትመራው ፖላንድ በዓለም ዋንጫው ለዘጠነኛ ጊዜ ለመሳተፍ ነው ወደ መጨረሻው ዙር ያለፈችው።

በሌላ በኩል ስዊድን ደግሞ ከአራት ዓመት በፊት በሩሲያው የዓለም ዋንጫ እሩብ ፍጻሜ መድረስ የቻለች ሲሆን በወቅቱ በእንግሊዝ 2 ለባዶ ተሸንፋ ነው ከውድድሩ የተሰናበተችው።

የኳታሩ የዓለም ዋንጫ እንዳያመልጠው በሚፈልገው ዝላታን ኢብራሂሞቪች የምትመራው ስዊድን ከቼክ ሪፐብሊክ ትልቅ ፈተና ይጠብቃታል።

የዓለም ዋንጫን አራት ጊዜ ያነሳችው ጣልያን የሌለችበት ውድድር ልናይ ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው። የአውሮፓ ዋንጫን ሳትጠበቅ ያሸነፈችው ጣልያን አሁን ላይ ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ነች።

ከኖርዝ ማሴዶኒያ ጋር የተደለደለችው ጣልያን ይህንን ጨዋታ የምታሸንፍ ከሆነ በመጨረሻው ዙር ከፖርቹጋል አልያም ከቱርክ አሸናፊ ጋር ትገናኛለች።

የክርስቲያኖ ሮናልዶ ፖርቹጋል ደግሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው በቀጥታ የማለፍ ዕድሏን የተነጠቀችው።

ከሰርቢያ በነበራቸው የመጨረሻ ጨዋታ አቻ ይበቃቸው የነበረ ቢሆንም ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባቸው ግብ ሁለት ለአንድ ተሸንፈው አሁን ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛሉ።

ሐሙስ ምሽት ከቱርክ የምትጫወተው ፖርቹጋል ይህንን ጨዋታ ካሸነፈች ከጣልያን እና ሰሜን ሜሲዶኒያ አሸናፊ ጋር ትገናኛለች።