"በየ11 ደቂቃው አንዲት ሴት በአጋሯ ወይም በዘመዷ ትገደላለች" ተመድ

የፎቶው ባለመብት, Ravikiran Rajagopal / EyeEm
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በየ11 ደቂቃው አንድ ሴት በፍቅር አጋሯ ወይም የቤተሰብ አባል በሆነ ዘመድ እንደምትገደል ገለጹ።
ከሁሉ የከፋው ደግሞ በአብዛኛው ግድያው የሚፈጸመው ሴቶች "እጅግ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው" ብለው በሚያምኑት መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነው።
በመላው ዓለም ከሦስት ሴቶች አንዷ ጥቃት ደርሶባት እንደሚያውቅም ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል።
በየዓመቱ በሚካሄደው ሴቶች ባሉበት ሁኔታ ዙሪያ (Status of Women) በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር፣ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት "የዓለም ረዥሙና አሳሳቢው ወረርሽኝ" ነው ብለዋል።
ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለማስወገድ የወንዶች ሚና ምን መሆን እንዳለበት በመድረኩ ውይይት ተደርጓል።
"ጥቃትን ለመግታት የመጀመሪያው እርምጃ የወንዶችን ልብ እና አእምሮ መለወጥ ነው። ችግሩን የፈጠሩት ወንዶች ናቸው። ችግሩን ማቆም የሚችሉትም ወንዶች ናቸው" ብለዋል ዋና ፀሐፊው።
ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር እያንዳንዱ ወንድ "መስታወት ፊት ቆሞ የወንዶች የበላይነትን ከሥር መሠረቱ ነቅሎ ለማስወገድ ቃል መግባት አለበት" ሲሉ ተደምጠዋል።
አያይዘውም "አደገኛ የወንድ የበላይነት ስሜትን ለማስወገድ፣ ባህል የጫነውን የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍ እንዲሁም ለዘመናት ለጥቃት መንስኤ የሆነውን መድልዎ ለመግታት እያንዳንዱ ወንድ ለእራሱ ቃል መግባት አለበት" በማለት ተናግረዋል።
ጾታዊ ጥቃትን ለመግታት የተባበሩት መንግሥታት እስካሁን ድረስ 880,000 ወንዶችን ጤናማ ስለሆነ ወንድነት (positive masculinity) አስተምሯል።
እነዚህ ወንዶች ግጭትን በሰላማዊ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚችሉ እና ጤናማ ስለሆነ ግንኙነትም ትምህርት ተሰጥቷቸዋል።
ሆኖም ግን ከዚህም በላይ ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቁሟል።
የድርጅቱ አባል አገራት ጾታዊ ጥቃትን ለማቆም የአስቸኳይ ጊዜ ዕቅድ እንዲነድፉ ዋና ፀሐፊው ጉቴሬዝ አሳስበዋል።
ጾታዊ ጥቃትን በመዋጋት አፍሪካ መሻሻል እያሳየች ነው
የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) እና 'ኢኳሊቲ ናው' እንዳሉት አፍሪካ ጾታዊ ጥቃትን በመዋጋት መሻሻል ያሳየች አህጉር ናት።
በአህጉሪቱ የታየው መሻሻል ግርዛትን መቀነስንም ያካትታል።
የተለያዩ ዘርፎችን አጣምሮ በመሥራት እንዲሁም የየዘርፉን ባለድርሻ አካላት በማካተት የሴቶችን መብት ለማስከበር መሠራቱ በአፍሪካ ለውጥ እንዲመጣ አግዘዋል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው ሪፖርት 'ስፖትላይት' በተባለ ፕሮግራም11 የአፍሪካ አገሮችን ይዳስሳል።
ይህም ማንኛውንም ዓይነት ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃተን ለመግታት ያለመ ነው።
እነዚህ 11 አገራት ኢትዮጵያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጉያና፣ ኬንያ፣ ላይቤሪያ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል፣ ሴራ ሊዮን፣ ሶማሊያ፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ ናቸው።
ከ11ዱ አገራት ሰባቱ ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጋያና እና ሴኔጋል ግርዛትን በሕግ ከልክለው ለአተገባበሩ በጀት መድበዋል።
የተቀሩት የአፍሪካ አገራት ግን እስካሁን ድረስ ግርዛትን በሕግ አላገዱም።
የኢኳሊቲ ናው የጎጂ ድርጊቶች ማስቆም ክፍል ኃላፊ አሴናት ሚትሀይ "ግርዛት በሕግ እንዲታገድ፣ ፖሊሲ እንዲቀረጽ፣ ብሔራዊ ዕቅድ እንዲወጣ እና በጀት እንዲመደብ ጠንካራ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል" ብለዋል።












