የቻይናው አውሮፕላን አደጋ፡ የቤተሰብ አባላት መረጃ እየተጠባበቁ ነው

የአደጋ ጊዜ ሠራተኖች አደጋው ያጋጠመበት አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአደጋ ጊዜ ሠራተኖች አደጋው ያጋጠመበት አካባቢ
ታትሟል

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በደቡብ ቻይና ካጋጠመው የአውሮፕላን አደጋ በሕይወት የተረፉ ካሉ ፍላጋ ላይ ሲሆኑ የተጓዝ መንገደኞች ቤተሰበብ አባላትም መረጃ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ትናንት የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኤምዩ5735 አውሮፕላን 132 ሰዎችን ይዞ በጓንግዢ ግዛት መከስከሱ ይታወሳል።

ይህ የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ኩሚንግ ከተባለው ከተማ ወደ ጓንግዡ እየተጓዘ ሳለ ጓንግዢ ግዛት ውስጥ ወድቆ ከተከሰከሰ በኋላ በእሳት ተያይዟል።

አየር መንገዱ ከዚህ አደጋ በኋላ ሁሉንም ቦይን 737-800 አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ ማድረጉ ተዘግቧል።

አደጋው በመላው ቻይና ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን ፕሬዝደንት ዢ ዢንፒንግ የአደጋው ምንስኤ እንዲጣራ ሰፊ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የአደጋ ጊዜ ሠራቶች አደጋው ወደ ተከሰተበት ስፍራ ተሰማርተዋል።

እስካሁን ከአደጋው በሕይወት የተረፈ ሰው አልተገኘም። ሰዎችን በሕይወት የማግኘት እድሉም ጠባብ ነው እየተባለ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንገደኞች ቤተሰቦች እና ወዳጆች አደጋ ያጋጠመው አውሮፕላን መዳረሻ በነበረው ጉዋንዡ አየር ማረፊያ ተሰባሰበዋል።

ባለሥልጣናት እስካሁን ድረስ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎችን ማንነት ይፋ አላደረጉም።

አንድ ግለሰብ የሥራ ባልደረባው በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ እንደነበረ ለጋዜጠኖች ሲናገር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አንድ ግለሰብ የሥራ ባልደረባው በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ እንደነበረ ለጋዜጠኖች ሲናገር።

የቤተሰብ አባላት ከሰተበሰቡበት አየር ማረፊያ የሚወጡ ምስሎች በከባድ ሐዘን ውስጥ ሆነው መረጃ የሚጠባበቁ ሰዎችን አሳይቷል።

የበረራ ቁጥር ኤምዩ5735 በአየር ላይ ለአንድ ሰዓት ያክል የቆ ሲሆን፤ ወደ መዳረሻ እየተቃረበ ሳለ እየበረረ ከነበረበት ከፍታ በድንገት ዝቅ ብሎ ነበር። ይህ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሜትሮች ወርዷል።

የአውሮፕላኖችን በረራ የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 አውሮፕላኑ 29ሺህ100 ጫማ ላይ እየበረረ የነበረ ሲሆን ከ135 ሴኮንዶች በኋላ ግን ሲበር የነበረው በ9075 ጫማ ላይ እንደነበር አሳይቷል።

የቻይና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል ሆኖ ሲበር የሚያሳይ ምስል አሳይቷል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የበረራ መረጃ የሚመዘግበውን ብላክ ቦክስ እስካሁን ፈልገው እንዳላገኙ እየተዘገበ ነው።

በአሁኑ ጊዜ የቻይና አየር መንገዶች በአጠቃላይ አስተማማኝ የደኅንነት ሪኮርድ ያላቸው ሲሆን፣ የመጨረሻው ከባድ የተባለው አደጋ ያጋጠመው ከ12 ዓመታት በፊት ነበር።

በዚህ በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት በተከሰከሰ አውሮፕላን 42 ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ነበር።