ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ በተከሰተ የጸጥታ ችግር ሰዎች ተፈናቀሉ
በደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቆ በመግባት የአንድ ሰው ሕይወት ማጥፋቱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማፈናቀሉ ተገለጸ።
የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ኡገቱ ኦዲንግ በደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀስውና እና በእንግሊዘኛ መጠሪያው 'ሳውዝ ሱዳንስ ፒፐል ሊብሬሽን ሙቭመንት ኢን ኦፖዚሽን' ተብሎ የሚጠራው ቡድን ወደ ክልሉ ዘልቆ በመግባት የአንድ ሰው ከመግደሉ በተጨማሪ ስድስት ሰዎችን አቁስሏል።
የደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን ጥቃትን ተከትሎም በተፈጠረው ስጋት ከ9 ሺህ ባላይ ሰዎች ከአጎራባች ቀበሌዎች በመልቀቅ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ ኡገቱ አዲንግ በደቡብ ሱዳን መንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል በተከሰተው ግጭት ምክንያት ባለፈው ማክሰኞ ታጣቂዎቹ "ድምበር አልፍው በመግባት" በኑዌር ዞን በላሬና በጂካዎ ወረዳዎች ውሰጥ ባሉ አራት ቀበሌዎች ዘረፋ መፈጸማቸውንም አመልክተዋል።
"በሕግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት [በትግራይ ክልል በነበረው]" በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ በኩል በቂ የፀጥታ ኃይል እንዳልነበረና "ውስን" የፌዴራል ፖሊስ አባላት ብቻ እንደነበሩ የጠቆሙት ኃላፊው "የነበረው ችግር በእኛ ኃይል ማቆም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ነበር" ብለዋል።
እንደ ኃፊው ገለጻ ከሆነ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ግን የፌዴራሉና የክልሉ ኃይሎች "ድንበር አልፈው የገቡ ታጣቂዎችን ወደ ራሳቸው ግዛት እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ሰርተዋል።"
የክልሉም ይሁን የፈዴራል የፀጥታ ኃይሎች ከታጣቂዎቹ ጋር ምንም አይነት የተኩስ ለውውጥ እንዳለደረጉ ኃላፊው አመላክተዋል።
ሆኖም በደቡብ ሱዳን በኩል በተቀናቃኞቹ መካከል በድንበር አቅራቢያ በነበረው የከባድ መሳሪያ ተኩስና በ"ተባራሪ ጥይት" በደረሰው ጉዳት በፈጠረው ስጋት በአራቱ ቀበሌዎች የነበሩ ከ9 ሺህ በላይ ስዎች መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ሰዓት በቂ የፀጥታ ኃይል በመሰመራቱ እና ታጣቂው ቡድን በደቡብ ሱዳን መንግሥት ኃይል "ተሸንፎ በማፈግፈጉ" አካቢው መረጋገቱን ገልጸዋል።
"ይህ ቡድን ከእኛ ግዛት ውጪ ያለ በመሆኑ የለም ብሎ መደምደም አይቻልም። በአሁን ጊዜ ግን ግዛታችን ከዚህ ጦርነት ነጻ ለማድረግ ችለናል" ሲሉ የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በችግሩ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አጎራባች ቀበሌዎች መሸሻቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፤ "ወንዶች ወዲያው ወደ መንደራቸው ቢመለሱም" ህጻናት እና ሴቶች ግን ወደ መኖሪያቸው እንዳልተመለሱ ገልጸዋል።
የነዋሪዎቹ ምግብን ጨምሮ ንብረቶቻቸው በመዘረፉ መልሶ ለማቋቋም እና ወደ ቀያቸው ለመመለስ መንግሥት መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር አብሮ እየሰራ ነው ሲሉ አቶ ኡገቱ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች የሙሩሌ ጎሳ አባላት ዘልቀው በመግባት ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ዘረፋዎች ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል።