በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች የዜጎቿን ሕይወትን እንዴት ቀየሩት?

ታትሟል

ሩሲያ በዩክሬን በፈጸመችው ወረራ ምክንያት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ሕብረት ታይቶ የማይታወቅ የፋይናንስ ማዕቀብ ሲጥሉባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ደግሞ አገሪቱን ለቀው ወጥተዋል።

የማዕቀቦቹ ጉዳት በተራ ዜጋው ላይ መታየት ጀምሯል።

ይህ ምዕራባውያኑ በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ፤ የመሠረታዊ ምርቶች ዋጋን እያሻቀበ፣ ሥራ የማጣት አደጋ እየተደቀነ እንዲሁም ለአንዳንዶች ከተቀረው ዓለም የመገለል ስሜትን እየፈጠረ ነው።

የዕለት ተዕለት ኑሮ እየተቀየረ የመጣባቸው አንዳንድ መንገዶች እንቃኛለን።

የምግብ ዘይት፣ ስኳር እና የደም ግፊት መድኒት

በወረራው የመጀመሪያ ሳምንት የሸቀጦች ዋጋ 2.2 በመቶ ጨምሯል። ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ ካሳዩት መካከል ምግብ ተጠቃሽ ነው።

የምግብ ሸቀጦችን የማከማቸት ዜናዎች ከተሰሙ በኋላ አንዳንድ ነጋዴዎች ሽያጫቸውን ገድበዋል። መድኃኒት ላይ ማዕቀብ ባይጣልም፤ የመርከብ ኩባንያዎች አገልግሎታቸውን በማቋረጣቸው መድኃኒት የማግኘት ዕድሉን ያጠበዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የሩብል (የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ) በማሽቆልቆሉ ብዙ ቸርቻሪዎች ዋጋ እንዲጨምሩ አድርጓል።

በማዕከላዊ ሞስኮ የምትኖረው ዳሪያ "ምግብ ባይጠፋም በጣም ውድ ይሆናል" ትላለች። "ምን ያህል ውድ ነው? መገመት አልችልም። ለማሰብ እንኳ እፈራለሁ።"

ጃን በሞስኮ የሚኖር እና የሚሰራ የአውሮፓ ሕብረት ዜጋ ነው። የካቲት 20 ለአስቤዛ 5,500 ሩብል (57 ዶላር) ወጪ አድርጓል። "አሁን ለተመሳሳይ አስቤዛ 8,000 ሩብል ያስከፍላል" ይላል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት የወተት ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል ይላል።

የስኳር እና የእህል ዋጋ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው በ20 በመቶ ንሯል። የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል ታስ አንዳንድ ቸርቻሪዎች በዋና ዋና ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪን በአምስት በመቶ ለመገደብ ተስማምተዋል ብሏል። ሌሎች ደግሞ ደንበኞች እንደ ዱቄት፣ ስኳር እና ዘይት ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች የሚገዙበትን መጠን እየገደቡ ነው።

ዳሪያ እያከማቸች ነው። "4 ኪሎ ግራም ቡና፣ 8 ሊትር ዘይት እና አራት ጠርሙስ ውስኪ ገዝተናል" ለደም ግፊትዋ ለሦስት ወር የሚበቃት መድኃኒት እንዲሰጣት አዝዛለች - አንዳንድ መድኃኒቶች ቀድሞውንም ለመያዝ በጣም ከባድ እንደሆኑ ትናግራለች።

የመጨረሻዎቹ አይፎኖች እና የመጨረሻ 'የውጭ ጉዞ' ዕድል

አንዳንድ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የዘመናዊ ስልኮች እና የቴሌቪዥኖች ዋጋ ከ10 በመቶ በላይ ጨምሯል።

ወደ ቱርክ የሚደረግ የሽርሽር ጉዞ በአማካይ በ29 በመቶ ጨምሯል። እንደ አፕል፣ አይኪያ እና ናይኪ ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ከእንግዲህ ሩሲያ ውስጥ ምርታቸውን አይሸጡም።

አፕል ከመጋቢት 2 ጀምሮ በሩሲያ ውስጥ ቀጥታ የምርት ሽያጭ እንደሚያቆም አስታውቋል። ዳሪያ "አሁን ሁላችንም የያዝነው የመጨረሻችንን አይፎን ስልክ ይሆናል የሚል ሃሳብ አለ" ትላለች።

ዳሪያ ለቤተሰቧ አዳዲስ ላፕቶፖች ለመግዛት እያሰበች ስለነበር የዋጋ ጭማሪ እያየለ በመሄዱ ግዢውን በችኮላ ፈጽማለች።

"በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ 70,000 ሩብል [730 ዶላር] ገደማ የነበሩት ላፕቶፖች በወሩ መገባደጃ ላይ 100,000 ሩብል ደርሰዋል። ላፕቶፖቹ ተሽጠው ከማለቃቸው በፊት ዋጋቸው 140,000 ሩብል ደርሶ ነበር።"

የአዳዲስ መኪኖች ዋጋም ጨምሯል። "መኪናው ጥገና በሚፈልግበት ጊዜ የሚያስፈልግ መለዋወጫ እና ዘይት ገዝተናል። ዓይናችን እያየ ዋጋው በእጥፍ ከመጨመሩ በፊት በቀድሞው ዋጋ መግዛት ችለናል" ትላለች ዳሪያ።

የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ፓቬል ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን በሞስኮ ለሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ዕቃዎችን ለመግዛት ይፈልግ ነበር።

ጦርነቱ በተጀመረበት ቀን የአንዳንድ ዕቃዎች ዋጋ 30 በመቶ ሲጨምር ተመልክቷል። ፍሪጅ፣ ማብሰያ፣ ማጠቢያ ማሽን እና ማንቆርቆሪያ መግዛት ችሏል።

አይኪያ ከመዘጋቱ ከአንድ ቀን በፊት አልጋ እና ቁምሳጥን አዝዞ ነበር። የአይኪያ ዋጋዎች ተለውጠዋል ብሎ አያስብም።

ማክዶናልድስ የነበሩትን 847 ሬስቶራንቶቹን የመዝጋቱ መልዕክት ለሩሲያውያን ማስተላለፉ አይዘነጋም። ከ30 ዓመታት በፊት ሶቭየት ሕብረት እያለች ከተከፈቱት የመጀመሪያዎቹ የምዕራባውያን ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነበር።

የማክዶናልድስ የመዘጋቱ ዜና በተነገረ በሰዓታት ውስጥ ከማክዶናልድስ ገዝተው የሚሸጡ የሩሲያውያን ምግብ ቤቶች ከተለመደው ዋጋ እስከ 10 እጥፍ ለመሸጥ ማስታወቂያዎችን አስነግረዋል።

አንዱ ማስታወቂያ "ማክዶናልድ ከመዘጋቱ በፊት የተገዙ ምግቦች እና ኬኮች አሉን። ምገቡን ለማጣጣም የመጨረሻ እድላችሁ ነው" ይላል።

ደንበኞችን ማጣት

የሩሲያ ባንኮች ከስዊፍት ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ታግደዋል። ቪዛ፣ ማስተርካርድ፣ አሜሪካን ኤክስፕረስ፣ አፕል እና ጎግል ፔይ በሩሲያ ያላቸውን አገልግሎት ገድበዋል።

በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ኢንዱስትሪ የተሰማራችው ናታሻ "ሁኔታው በሥራችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። የደንበኞቻችን ቁጥር ቀንሷል። አንዳንዶች የአባልነት ክፍያቸውን እንድንመልስላቸው እየጠየቁን ነው። የቤት ኪራይ፣ የመሳሪያ እና የጽዳት ወጪያችን እየጨመረ ነው። ከማዕቀቡ በኋላ ወጪው በአማካይ በ30 በመቶ ጨምሯል" ትላለች።

እንደ እሷ ያሉ ብዙ የንግድ ተቋማት እንደሚዘጉም ትገምታለች። የማይቸገሩት ከውጭ የሚገቡ መሳሪያዎችን ከሩሲያ አምራቾች ማግኘት የሚችሉት ናቸው።

በርካታ የቋንቋ ትምህርት ቤቶችን የምትመራው ኤካተሪና በበኩሏ ማዕቀቡ ከወዲሁ ችግሮችን እንደጋረጠባት ትናገራለች።

"ሁሉም የገንዘብ ማስተላለፊያ ኔትዎርኮች ስለታገዱ በውጭ ለሚገኙ መምሀራኖቻችን መክፈል አንችልም። በተጨማሪም በአሜሪካ፣ በጀርመን እና በላትቪያ ያሉ ተማሪዎቻችንም ወደ አካውንታችን ገንዘብ ማስገባት አልቻሉም። ችግሩን ለመፍታት መንገዶች አግኝተናል" ሆኖም በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዱ የሥራ ቀን የሚጀምረው አዲስ ፈተናን በመጋፈጥ ነው።

ዙም ከታገደ ዓለም አቀፍ የቡድን ትምህርታቸውን እንዴት ማስቀጠል እንደሚችሉ ኤካተሪና ያሳስባታል።

የበይነ መረብ ሥራዎቿም የሚጠገኑት በዩክሬን በሚገኝ ኩባንያ ስለሆነ ችግሮች እንዳጋጠሟት ተናግራለች።

ናታሻ ከለውጦቹ ጋር ለመስማማት አስቸጋሪ እየሆነባት ነው። "ይህ ሁላችንም የጠፋን እና ግራ እንድንጋባ የሚያደርግ ሙሉ ለሙሉ አዲስ አይነት ቀውስ ነው። በሥራ ብቻ ሳይሆን በራሳችን ህይወት ውስጥ ጭምር ነው። የገቢ ማጣት፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ግንኙነቶች መቀነስ እና በውጭ አገር የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻችንን ለማየት ለመጓዝ አለመቻል ተፈጥሯል። ቀደም ሲል ያጣናቸው እና እስካሁን ሙሉ በሙሉ ያልተረዳናቸው ብዙ ነገሮችም አሉ።"

ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከሩሲያ ሲወጡ ስለ ሥራ ማጣት መስማት እንዳስጨነቃት ዳሪያ ትናገራለች። "እስካሁን በምሠራቸው በመንግሥት በሚደገፉ ፕሮጀክቶች ላይ ምንም አይነት ቅነሳ የለም። ነገር ግን ሥራዬን እንዳላጣ በጣም እፈራለሁ" ትላለች።

የመገናኛ ብዙን መዘጋት እና የቀዝቃዛው ጦርነት ትውስታዎች

የክሬምሊን መንግሥት ከወረራው ጋር በተያያዘ "ሐሰተኛ " ዜና አሰራጭቷል ተብሎ የታሰበውን በእስር እንደሚቀጣ አስታውቋል።

ገለልተኛ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ከ13,000 በላይ ሰዎች በፀረ-ጦርነት ሰልፎች ላይ በመሳተፋቸው ታሰረዋል።

ዳሪያ ለማዕቀቡ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ተጠያቂ ታደርጋለች። አብዛኛዎቹ ሩሲያውያን ግን ዜና የሚያገኙት ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲሆን የሚያሰራጨውም የክሬምሊንን ፀረ-ዩክሬን ፕሮፓጋንዳ ነው።

ሌሎች ጦርነቱን ባይቀበሉም በዝምታ ውስጥ ናቸው። ለሩሲያውያን መሪያቸውን መተቸት ዋጋ ያስከፍላል። ምዕራባውያን መንግሥታት በሩሲያውያን ላይ የተከመረው ማዕቀብ ለውጥ ያመጣል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

ባለሃብቶቹ ሩሲያውያን ብቻ የማዕቀቡ ህመም ይሰማቸዋል የሚለው አመለካከት አከራካሪ ነው። ማንም ሰው ቀጥሎ ስለሚመጣው በእርግጠኝነት አያውቅም። የኢኮኖሚ ውድቀቱ ግን ከባድ እና ረዥም ጊዜ የሚቆይ እንደሚሆን ይጠበቃል። የሩስያ ማዕከላዊ ባንክ ከወረራው በኋላ "ከባድ" የኢኮኖሚ ለውጥ ታይቷል ብሏል።

ዳሪያ እንደምትለው ላይ ላዩን ሞስኮ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ አይገምቱ ይሆናል። የከተማዋ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ሙሉ ናቸው። የከተማው ባቡር እየሠራ ነው። መሀል ከተማ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ አልቀነሰም።

የዛሬዎቹ ክስተቶች ከሶቭየት ኅብረት መፈራረስ በኋላ እአአ በ1990ዎቹ የሩስያ ኢኮኖሚ የነበረበትን ትዝታ ይቀሰቅሳል።

"በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ያሉ እና በእነዚያ ጊዜያት ከነበሩ ሰዎች ጋር መነጋገር እና ለምግብ መውሰጃ ስለሚሰጠው ካርድ መነጋገር አስደሳች ነበር። ስኳር፣ ቅቤ እና ቮድካ ለመግዛት ኩፖኖች ነበሩን" ትላለች ዳሪያ።

"በድህነት መጨመር እና በሥራ ማጣት ምክንያት ሌብነት እና ዝርፊያ እንዳይጨምር እሰጋለሁ" ትላለች።