በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድ መንግሥት አስታወቀ

የኢትዮጵያ ካርታ
ታትሟል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ እንደተፈጸመ የተገለጸውን አሰቃቂ ድርጊት አጣርቶ በፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መንግሥት አስታወቀ።

ከትናንት ጀምሮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወር የነበረው አሰቃቂ ተንቀሳቃሽ ምስል ቁጣና ውግዘትን የቀሰቀሰ ሲሆን በርካቶች መንግሥት በድረጊቱ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ እየጠየቁ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ መፈጸሙን አመልክቶ "እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ" ሲል አውግዞታል።

በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ በስፋት የታየው በተንቀሳቃሽ ምስል የፀጥታ ኃይሎች የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች በህይወት ያሉ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ሲያደረጉ የሚያሳይ ነው።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የአሰቃቂው ድርጊት ሰለባ የሆኑት ግለሰቦች ማንነት የማይታይ ቢሆንም ድርጊቱን የሚፈጽሙት ሰዎች ገጽታ በተወሰነ ደረጃ ይታያል።

በተጨማሪም ይህንን ሁኔታ የሚመለከቱ ሰዎች በአካባቢው እንዳሉ ቪዲዮው ላይ በተጨማሪ ይታያል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው ድርጊቱ "ከማንኛውም የሰብአዊነት እሳቤ ያፈነገጠና እጅግ አሰቃቂ ወንጀል ነው" ሲል ያወገዘው ሲሆን፣ ጨምሮም የድርጊቱ "መነሻም ሆነ ማንነት ምንም ይሁን ምን መንግሥት ይህን አይነት ፍጹም ከሰብአዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትን የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል" ብሏል።

ይህንን ክስተት በተመለከተ ከቤኒሻልጉል ጉሙዝ ክልል ባለሥልጣናት በኩል እስካሁን የተሰጠ ምንም መግለጫ የለም።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአገሪቱ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ካላባቸው አካባቢዎች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ሳቢያ በተለያዩ ጊዜያት በርካቶች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በተጨማሪም በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች እዚያው ክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጪ በአጎራባች ክልሎች ውስጥ ተፈናቅለው ይገኛሉ።

ባለፈው ሳምንት እነዚሁ ታጣቂዎች በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አሁን ባወጣው መግለጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን "ሕገ ወጥነት ለመቆጣጠርና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል" ከክልሉና ከፌደራል መንግሥቱ የተወጣጡ የፀጥታ አካላት በጋር እየሰሩ መሆናቸውን አመልክቷል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የተከሰቱ ጥቃቶችን እና መፈናቀሎችን ተከትሎ በርካታ የክልሉ አካባቢ በክልሉ እና በፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት በሚመራ የዕዝ ማዕከል [ኮማንድ ፖስት] እየተዳደረ ይገኛል።