ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ እና ልጆቻቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና ሁለት ልጆቹ ኒው ዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ በመፈጸም ጥያቄዎችን መመለስ አለባቸው ሲሉ አንድ ዳኛ ብይን አስተላልፈዋል።
ትራምፕ የሚያስተዳድሩት ድርጅት አሳሳች እና ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የግብር እፎይታ እንዲሁም ብድር እንዲያገኝ ተደርጓል ሲሉ የኒው ዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሰዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በ21 ቀናት ውስጥ ቃለ መሃላ ፈጽመው ቃላቸውን መስጠት ይኖርባቸዋል።
ትራምፕ የሚቀርብባቸውን ክስ በሙሉ የሚቃወሙ ሲሆን ውሳኔውን ለማስቀልበስም እንደሚሰሩ ይገመታል።
በሌላ በኩል ደግሞ በምንም ጉዳይ ላይ አስተያየት ያለመስጠት መብታቸውን መጠቀም ይችላሉ ዶናልድ ትራምፕ።
የትራምፕ ድርጅት ለቢቢሲ በላከው ምላሽ ላይ "አጠቃላይ ስርዓቱ በሙስና ተመሰቃቅሏል'' ብሏል።
ሐሙስ ዕለት የኒው ዮርክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አርተር ኢንጎሮን ዶናልድ ትራምፕ፣ ወንድ ልጃቸው ትራምፕ ሁለተኛ እና ሴት ልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገዛት አለባቸው ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የተጀመረውን የፍርድ ሂደት በፖለቲካዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተና ምንም ግብ የሌለው ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን ይሰጣሉ ወይ የሚለው ጉዳይ ጊዜ የሚፈታው ይመስላል። ምናልባትም በይፋ ተቃውሟቸውን ሊያሰሙ ይችላሉ። ካልሆነ ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ምንም አይነት አስተያየትም ሆነ መልስ ከመስጠት ሊቆጠቡ ይችላሉ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠበቆችም ቢሆኑ ይህንን አማራጭ ነው እያቀረቡ የሚገኙት። ነገር ግን ድርጅታቸውን ትልቅ ደረጃ ማድረስ ለቻሉት ዶናልድ ትራምፕ ይህን መሰል ክሶች ጥሩ ጅማሮ አይመስልም። ለወደፊቱም እንደዚህ አይነት ክሶችን ለመከላከል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።
በአውሮፓውያኑ 2019 የተጀመረው ይህ የክስ ሂደት ዶናልድ ትራምፕ ከመንግሥት የሚያገኙትን ብድር ከፍ ለማድረግ ሲሉ የሌላቸውን ሀብት አስመዝግበዋል፤ ያላቸው የንብረት ዋጋ ከመጠን በላይ ከፍ እንዲል አድርገዋል የሚል ነው። በክሱ መሰረት ይህ የሆነው ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት ነው።