የፈረንሳዩ ማክሮን 'ፑቲን ሁኔታዎችን ለማርገብ ቃል ገብተውልኛል' አሉ

ቮሎድሚር ዘለንስኪና ኢማኑኤል ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቮሎድሚር ዘለንስኪና ኢማኑኤል ማክሮን
ታትሟል

ለከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ወደ ሩሲያና ዩክሬን ያቀኑት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቭላድሚር ፑቲን ሁኔታዎችን እንደሚያረግቡ ቃል እንደገቡላቸው ተናገሩ፡፡

"ድንበር አካባቢ ሁኔታዎች እንደማይባባሱ፣ አዳዲስ ትንኮሳዎች እንደማይኖሩ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ" ብለዋል ማክሮን ለጋዜጠኖች፡፡

ኢማኑኤል ማክሮን ይህን ያሉት የዩክሬንኑን አቻቸውን ከማግኘታቸው ቀደም ብሎ ነው፡፡

ሩሲያ ዩክሬን ድንበር ላይ መቶ ሺህ ወታደሮቸን ማስፈሯ ሲነገር ነበር፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሩሲያ ወረራውን ለመፈጸም ከሚያስፈልጋት ኃይል 70 ከመቶው በዩክሬን ድንበር ላይ መስፈሩን አረጋግጠናል ያሉት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

ይህ በዩክሬን፣ ሩሲያና ምዕራብ አገራት መካከል ከፍተኛ የጦርነት ስጋትና ውጥረት የተከሰተው ሩሲያ በደቡብ ዩክሬን የክሪሚያን ባሕረ ገብ በኃይል ከያዘች ከ8 ዓመት በኋላ ነው፡፡

ሞስኮ፣ ዩክሬን የሚንስክ ስምምነትን ልታከብርልኝ አልቻለችም ስትል ትወቅሳታለች፡፡

የሚንስክ ስምምነት የሚባለው ጀርመንና ፈረንሳይ ያሸማገሉትና በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተደረሰ የሰላም ስምምነት ነው፡፡

ሩሲያ የምትደግፋቸው አማጺያን በሚቆጣጠሩት አካባቢ ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ 14ሺህ ሰዎች መገደላቸው ይነገራል፡፡

ማክሮን ትናንት ማክሰኞ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪያቭ የተገኙ ሲሆን ወደዚያ ያመሩት ሰኞ ዕለት ከፑቲን ጋር ቢያንስ ስድስት ሰዓታትን የፈጀ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡

ይህ የተራዘመ ውይይት የተደረገው በእራት ግብዣ ታጅቦ ነበር፡፡

ማክሮን ከፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር በሰጡት የጣምራ መግለጫ ይህን ውጥረት ለማርገብ ወደ ተጨባጭ መፍትሄ ማምራት አለብን ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው ፑቲን በተጨባጭ ጦርነቱን የማርገብ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡

"ቃላትን ብዙም አላምናቸውም፤ ፖለቲከኞች የሚጨበጥ እርምጃዎችን በግልጽ ሲወስዱ ነው የሚሻለው" ሲሉ ከባላንጣቸው ፑቲን የሰላም ተግባር እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል፤ ዘለንስኪ፡፡

ማክሮን ከዚህ በኋላ ወደ ጀርመን ያቀኑ ሲሆን በዚያ ጀርመንና ፖላንድ ለዩክሬን ሉአላዊነት ያላቸውን ቀናኢነት ገልጠውላቸዋል፡፡

እነዚህ መሪዎች በጀርመን የተገኙት የዌይማር ትሪያንግል ቡድን ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ነው፡፡

ይህ ቡድን የተመሠረተው የዛሬ 31 ዓመት ገደማ ሲሆን የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ አውሮጳን የሚገጥማትን አዳዲስ ፈተናዎች ለማርገብ የተፈጠረ ስብስብ ነበር፡፡

የአሜሪካው ጆ ባይደን በበኩላቸው ከትናንት በስቲያ ሰኞ አንጌላ መርክልን የተኩትን የጀርመኑን መራሒ መንግሥት ሾልዝን በዋሺንግተን ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ዋንኛ አጀንዳ ያደረጉት የሩሲያን የወረራ ስጋት ሲሆን ፑቲን እንደተፈራው ዩክሬንን የሚወሩ ከሆነ ወደ ጀርመን የተዘረጋውና ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ ፈሶበታል የሚባለውን የኖርድ ስትሪም2 የጋዝ መስመርን ለመዝጋት ዝተዋል፡፡

ይህ የሚፈራው ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀርመን ወታደር እንደማታዋጣ ቀደም ብላ ማሳወቋ በወዳጅ አገራትን ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር፡፡

ቭላድሚር ፑቲን ይህ የጦርነት ስጋት ጨርሶውኑ እንዲቀለበስ ያቀረቡት ቅድመ ሁኔታ በብዙ የምዕራብ አገራት ዘንድ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ሞስኮ፣ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዩክሬንን አባል ላለማድረግ እንዲወስን፣ እንዲሁም በምሥራቅ አውሮጳ አካባቢ ዝር እንዳይል ትፈልጋለች፡፡

አሁን በማክሮን የዲፕሎማሲ ሩጫ የሩሲያና የዩክሬን የድንበር ጦርነት የረገበ ቢመስልም ዘለንስኪ ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ተስተውሏል፡፡

ዘለንስኪ ከማክሮን ጋር በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ፑቲን የሚናገሩትን እምብዛምም እንደማያምኑ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

"ግልጽነት በመሪዎች ዘንድ ሲታይ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ማዘናጊያ ቁማር መሆን የለበትም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

በዚህ መግለጫ ላይ ያልተጠበቀ ሐሳብ የሰነዘሩት ማክሮን የዩክሬንና የኔቶ ግንኙነት የፊንላድን ሊመስል እንደሚችል ጥቁምታን ሰጥተዋል፡፡

"ፊንላንድ የኔቶ አባል ባትሆንም ቅርብ ናት" ብለዋል፡፡ ይህ ሐሳብ ዘለንስኪን ቅር ሳያሰኛቸው አልቀረም፡፡

ማክሮን በዲፕሎማሲ ጥረታቸው ከፑቲን ቃል አግኝቻለሁ ቢሉም ክሬምሊን ይህን ሐሳብ ለማስተባበል ጊዜ አልወሰደበትም፡፡

"ማክሮን የኔቶ መሪ አይደሉም፡፡ የተደረሰ ስምምነትም የለም" ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡

አሁንም በአገራት መካከል በየአቅጣጫው ንግግሩ የቀጠለ ሲሆን ሩሲያም ወደ ድንበር ወታደሮችና ቁሳቁስ ማስጠጋቷን ገፍታበታለች፡፡

ኔቶም ወደ ምሥራቅ አውሮጳ መስፋፋቱንና ለጦርነት የተጠንቀቅ መሰናዶ ማድረጉን ቀጥሎበታል፡፡