የደቡብ ሱዳን ስርወ መንግሥት ከ117 ዓመታት በኋላ ተመለሰ

የፎቶው ባለመብት, Daniel Badagbue Rimbasa
ታትሟል
በደቡብ ሱዳን ጥንታዊ ከነበሩት ስርወ መንግሥታት መካከል አንዱ የሆነው ከ117 ዓመታት በኋላ ተመለሰ።
የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ከሞቱም ከ100 ዓመታት በላይን አስቆጥረዋል።
ንጉሥ ጉቡዴ የተገደሉት በአውሮፓውያኑ 1905 በብሪታንያ መኮንኖች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ስርወ መንግሥቱን እንዲያስቀጥሉ የተደረጉትም የጉቡዴ የልጅ ልጅ ናቸው።
በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለትም የአዛንዴ ንጉሥ ሆነው ተሰይመዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም የአዲሱን ንጉሥ ዊልሰን ፔኒ ሪኪቶ ጉቡዴ የሲመት በዓል ለመታደም መገኘታቸውን ወንድማቸው በምዕራብ ኢኳቶሪያ፣ በያምቢዮ ግዛት ከሚገኘው ቤተ መንግሥት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሌሊቱን ጨምሮ በዚህ ሳምንት ሁሉ በዓላት ይኖራሉ" ብለዋል ልዑል ዳንኤል ባዳግቡኤ ሪምባሳ።
ልዑሉ አክለውም በአዛንዴ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ጠቃሚ ወቅት ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
"ባህላችንን ወደነበረበት መመለስ እና በማኅበረሰባችን መካከል ሰላማዊ አብሮነትን ማሳደግ አለብን" ሲሉ አክለዋል።
ልዑሉ፣ አዛንዴ በምዕራብ ኢኳቶሪያ ውስጥ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ስርወ መንግሥቱን እንደገና ለማቋቋም ግፊት ማድረጉን አስተባብለዋል።
"የዚህ ስርወ መንግሥት መመለስ ባህላችንን ለማስተዋወቅ ቅርሱን ለመጠበቅ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም"ብለዋል።












