ኡጋንዳ ለዲሞክራቲክ ኮንጎ 'ወረራ' 325 ሚሊዮን ዶላር እንድትከፍል ታዘዘች

የኡጋንዳ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ኡጋንዳ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት ውስጥ በነበራት ሚና ምክንያት 325 ሚሊዮን ዶላር እንድትከፍል ተወሰነ።

ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) በውሳኔው ኡጋንዳ እአአ ከ1998 እስከ 2003 ድረስ እንደ ወራሪ ኃይል ዓለም አቀፍ ደንቦችን ጥሳለች ብሏል።

ኡጋንዳ በምስራቅ ኢቱሪ ክልል ከ10,000 እስከ 15,000 ለሚደርሱ ሰዎች ሞት ምክንያት ነበረች ብሏል ፍርድ ቤቱ።

የኡጋንዳ ወታደሮች ወርቅ፣ አልማዝ እና እንጨት መዝረፋቸውም ታውቋል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 11 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፈላት ጠይቃ ነበር። ዳኞቹ አብዛኛውን ጥያቄዎች ውድቅ በማድረግ በጣም ዝቅተኛ መጠን ወስነዋል።

ኡጋንዳ ከ2022 እስከ 2026 በየዓመቱ 65 ሚሊዮን ዶላር እንድትከፍል አይሲጄ አዟል። የመጀመሪያው ክፍያ በመስከረም ወር ይፈጸማል።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተጠየቀችው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ምጣኔ ሐብቴን ያወድማል ስትል ኡጋንዳ ተከራክራለች። ፍርድ ቤቱ የተላለፈውን ውሳኔ "የኡጋንዳን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው" ብሏል።

ከ325 ሚሊየን ዶላር ውስጥ፦

  • 225 ሚሊዮን ዶላሩ በሰዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት
  • 40 ሚሊዮን ዶላሩ በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት
  • 60 ሚሊዮን ዶላሩ የተዘረፈውን ሃብት የሚሸፍን ነው።

ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ላይ "በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለደረሰው ጉዳት የሚሰጠው ካሳ ኡጋንዳ ዓለም አቀፍ ግዴታዋን በመጣሷ ምክንያት በግለሰብ እና በማህበረሰቦች ላይ የደረሰውን ጉዳት ያሳያል" ብሏል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ1999 በሃገሪቱ እና በዜጎቿ ላይ በተፈጸመ የጦር መሳሪያ ጥቃት በኡጋንዳ ላይ ክስ አቀርባለች። የኡጋንዳ ወታደሮችን በዘረፋ እና በሰብአዊ መብት ጥሰትም ተከሰዋል።

በማዕድን በበለጸገችው ምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ላለፉት አስርት ዓመታት ከፍተኛ ውድመት እያደረሱ ነው።

እአአ በ1990ዎቹ የኡጋንዳ እና የሩዋንዳ ወታደሮች ትልቋን ጎረቤታቸው ዲሞክራቲክ ኮንጎን ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር በመተባበር ሁለት ጊዜ ወረዋል።

ዓላማቸው ደግሞ መንግስትን ለመጣል ነበር። ድርጊታቸውንም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈጠረው ግጭት ወደ ድንበሮቻቸው እንዳይሸጋገር ጣልቃ ገብተናል ሲሉ ተከራክረዋል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይግባኝ የማይጠየቅበት እና የመጨረሻ ውሳኔ ነው። ሆኖም የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ውሳኔውን በአስገዳጅነት የሚያስፈጽምበት መንገድ የለውም።