ሴኔጋል ለእያንዳንዱ ተጫዋች ከ87 ሺህ ዶላር በላይና መሬት ሸለመች

የሴኔጋል ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ታትሟል

ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን ላመጡት የብሄራዊ ቡድኗ እያንዳንዱ ተጫዋች የገንዘብና የመሬት ሽልማት ሸለመች።

በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት በተካሄደው ስነ ስርዓትም እያንዳንዱ ተጫዋች ከ87 ሺህ ዶላር በላይ ሽልማትና በዋና ከተማዋ ዳካር እና በአጎራባቿ ዲያምኒያዲዮ ከተማ ውስጥ መሬት እንዲሰጣቸው ተደርጓል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ለቡድኑ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን የክብር ሽልማት (ኦርደር ኦፍ ዘ ላየን) የሰጧቸው ሲሆን በርካታ ደጋፊዎቻቸውም ከቤተ መንግሥቱ ውጭ በደስታ ጩኸታቸውን እያሰሙ ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል ቡድኑን የአፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ እና "ለአገሪቱም ክብር እና ኩራት በማስገኘት የህዝቡን ታላቅነት አስመስክረዋል" በሚልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

እንዲሁም የቡድኑን አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴንም አወድሰዋል።

አሊዩ ሲሴ "ጠንክረህና ጸንተህ ከሠራህ የምትፈልገውን እንደምታገኝ ያሳያል" ሲሉ ድሉን ገልጸውታል።

"በጣም ስሜታዊ ሆኛለሁ ምክንያቱም የሴኔጋል ህዝብ ይህን ዋንጫ ለ60 ዓመታት ናፍቋል" ብለዋል አሰልጣኙ።

ሴኔጋል በፍጻሜው ጨዋታ ግብፅን 4 ለ2 በመለያ ምት አሸንፋ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ሆናለች።

ጨዋታው በሁለቱ የሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔ እና መሐመድ ሳላህ መካከል የተደረገ ፍልሚያ ተብሎ በብዙዎች በከፍተኛ ጉጉት የተጠበቀ ነበር።

ጨዋታው ያለምንም ጎል በመጠናቀቁ ነበር ወደ መለያ ምት የተሸጋገረው።

ሴኔጋል ከዚህ ቀደም በሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች ከተሸነፈች በኋላ በመጨረሻም የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች።