ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ድመት ሲመታ የታየው የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋች ከፍተኛ ውግዘት ደረሰበት
ፈረንሳዊው ተከላካይ ኩርት ዙማ ድመት በእርግጫ እና በጥፊ ሲመታ የሚያሳይ ቪዲዮ መለቀቁን ተከትሎ የሚጫወትበትን ክለብ ጨምሮ በበርካቶች ተወግዟል።
ፖሊስ እና የእንስሳት መብት ተከራካሪዎች ጉዳዩን እየመረመርን ነው ብለዋል።
በድርጊቱ ይቅርታ የጠየቀው ዙማ ትናንት ምሽት በነበረው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ከዋትፎርድ ጋር ተሰልፏል።
በድርጊቱ የተበሳጩ ደጋፊዎች ዙማ በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ኳስ በነካ ቁጥር የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ ነበር።
የኤሴክስ ፖሊስ ከሮያል ሶሳይቲ ፎር ዘ ፕሪዘርቬዥን ኦፍ ክሩሊቲ ቱ አኒማልስ (አርኤስፒሲኤ) ጋር በመሆን "አስቸኳይ ምርመራዎችን በማካሄድ ላይ ነኝ" ብሏል።
ክለቡ ጉዳዩን በውስጥ በኩል እንደሚመለከተው አስታውቋል።
የዌስትሃም አሠልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ በማክሰኞው ጨዋታ ዙማን በቋሚነት ለማስጀመር ስለተወሰነው ውሳኔ "እሱ ካሉን ምርጥ ተጫዋቾቻችን አንዱ ነው። ጉዳዩ በክለቡ እየታየ ነው" ብለዋል።
የ27 ዓመቱ ዙማ "ለድርጊቴ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ከልቤ ለምጸጸትበት ምግባሬ ምንም አይነት ምክንያት የለኝም" ብሏል።
"በቪዲዮው ለተበሳጩ ሰዎች ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማኝ መግለጽ እፈልጋለሁ። ሁለቱ ድመቶቻችን ፍጹም ጤናማ መሆናቸውን ላረጋግጥላቸሁ እፈልጋለሁ።"
ጨምሮም "ድመቶቹ በመላው ቤተሰባችን የተወደዱ እና የተከበሩ ናቸው። ይህ ባህሪ እንደገና የማይደገም ክስተት ነው" ብሏል።
በዙማ ወንድም ዮአን እንደተቀረጸ በተነገረው እና መጀመሪያ በዘ ሰን በተለቀቀው ቪዲዮ ተጫዋቹ ጫማውን ወደ ድመቷ ሲወረውር እና ክፍል ውስጥ ሲያሳድዳት ያሳያል።
ተከላካዩን በክረምቱ ከቼልሲ በ29.8 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈረመው ክለቡ "ዌስትሃም ዩናይትድ የኩርት ዙማን ድርጊት በማያሻማ መልኩ ያወግዛል" ሲል ገልጿል።
"ከኩርት ጋር ተነጋግረናል። ጉዳዩን በውስጥ በኩል እንጨርሳለን። ነገር ግን በእንስሳት ላይ የሚፈጸመም ጭካኔ በምንም መልኩ እንደማንቀበል ግልጽ ማድረግ እንፈልጋለን።"
ክለቡ አክሎም "በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ዓይነት ጭካኔ በምንም መልኩ እንደማንቀበል እና ጉዳዩን በቁም ነገር እንደምንመለከተው ሙሉ በሙሉ ግልጽ ማድረግ እንፈልጋለን" ሲል አስታውቋል።
ዮአን ዙማም "በድርጊቴ ብቻ ሳይሆን ይህ ለብዙ ሰዎች ብስጭት እና ጭንቀት በፈጠረው ቪዲዮ ላይ በመሳተፌ በጣም አዝኛለሁ" ብሏል።
የኤሴክስ ፖሊስ ቃል አቀባይ "ከድመት ጋር በተያያዘ ማኅበረሰባችንን ሊያሳዝን የሚችል ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ እንዳለ እናውቃለን" ካሉ በኋላ፤ "ይህ ክስተት በኤሴክስ የተከሰተ ሊሆን ስለሚችል ምርመራዎች እንደቀጠሉ ናቸው" ብለዋል።
የእንስሳት መብት ተቆርቋሪው አርኤስፒሲኤ ደግሞ "ይህ በጣም የሚያናድድ ቪዲዮ ነው። ምርመራ እያከናወንን መሆኑን ልናረጋግጥ እንወዳለን" ብሏል።
"አሁን ተጨማሪ አስተያየት መስጠት ባንችልም ይህንን ጉዳይ እንድናውቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናችን ይድረስ።"
ኩርት ዙማ በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ማሄታ ሞላንጎ ተተችቷል።
"እሱን መቅጣት አንችልም። የሚቀጣው ቀጣሪው ነው። የእኛ ሚና ለተጫዋቹ ይህ ዓይነት ባህሪ ተቀባይነት እንደሌለው መንገር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።