አሜሪካ ስለ ካቡል የሽብር ጥቃት መረጃ ለሚያቀብል 10 ሚሊዮን ዶላር ልትሸልም ነው

ታትሟል

አሜሪካ በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰው የሽብር ጥቃት ጀርባ ያለውን አካል ለሚጠቁም ሁለት የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማቶች አዘጋጀች።

እአአ በነሐሴ 2021 በካቡል በደረሰው የቦምብ ጥቃት 13 አሜሪካውያን ወታደሮች እና 3 እንግሊዛውያንን ጨምሮ 185 ሰዎች ተገድለዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃት አድራሾቹን "አድነን እንይዛቸዋለን። አሜሪካ ይቅር አትላቸውም" ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለጥቃቱ ተጠያቂ የሽብር መሪው ሳናሁላህ ጋፋሪ እንደሆነ አስታውቋል።

ጋፋሪ የኢስላሚክ ስቴት ክንፍ የሆነውና በአፍጋኒስታን የሚንቀሳቀሰው አይኤስ-ኬ መሪ ነው።

ኬ የሚለው ቃል የሚወክለው ኮራሳን የተባለውን ጥንታዊ ታሪካዊ አካባቢ ነው። ይህ አካባቢ አሁን አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን ይገኙበታል።

ስለ ጋፋሪ እንዲሁም ስለ አይኤስ-ኬ መረጃ ለሚያቀብል ግለሰብ አሜሪካ ሽልማት እንደምትሰጥም አስታውቋለች።

አሜሪካ ሽልማቱን የምትሰጠው አዲስ በሠራችው "ሽልማት ለፍትሕ" በተባለ አሠራር ነው።

የአሜሪካ ወታደሮች ከወራት በፊት ከአፍጋኒስታን መልቀቃቸው ይታወሳል።

የአሜሪካ እርምጃ ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮበታል። የታሊባን ታጣቂዎች ወደ አፍጋኒስታን መዲና እንዲመለሱም በር ከፍቷል።

አሜሪካ እና አጋሮቿ ለዓመታት ሲያሠለጥኑት የቆዩት የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይል በታሊባን ተሽመድምዶ ወድቋል።

የ9/11 የሽብር ጥቃትን ተከትሎ አፍጋኒስታን የገባችው አሜሪካ በወቅቱ ታሊባንን ማስወገድ ችላ ነበር።

ለሽብር ጥቃቱ ተጠያቂ የሆነውና መሠረቱን አፍጋኒስታን ያደረገውን አል-ቃይዳ ለመዋጋት ነበር አሜሪካ ኃይሏን አፍጋኒስታን ያሰፈረችው።

አሜሪካ አፍጋኒስታንን ጥላ ስትወጣ በሐሚድ ካራዚ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የቦምብ ጥቃት ተሰንዝሯል።

ሸባብ አል ሙሐጂር በመባል የሚታወቀው ጃፋሪ አይኤስ-ኬን እንዲመራ ሰኔ 2020 ላይ ተሹሟል።

ለደረሰው የሽብር ጥቃት ተጠያቂ እንደሆነም የፀጥታ ኃይሎች ተናግረዋል።

የዲፕሎማቲክ ደኅንነት ተባባሪ ጸሐፊ ጀንትሪ ስሚዝ፤ አሜሪካ መረጃ ለሚሰጥ አካል የገንዘብ ሽልማት እንዳዘጋጀች ይፋ ባደረጉበት ወቅት "የሚሰጠን ጥቆማ አይኤስን ለማጥፋት እንዲሁም ግባቸውን በአጭሩ ለመቅጨት ይረዳናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

ጨምረውም "ፕሬዝዳንት ባይደን እንዳሉት ሁሉ አሸባሪዎቹን አሳደን እንይዛቸዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ባይደን የካቲት 3 ባደረጉት ንግግር በአሜሪካ የሰሜን ሶርያ ኦፕሬሽን የአይኤስ መሪ አቡ ኢብራሒም አል ቁራይሽ እንደሞተ አስታውቀዋል።

ይህ ግለሰብ ያለበትን ለሚጠቁም ሰው አሜሪካ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ ከዚህ ቀደም ተናግራ ነበር።

ገንዘቡ በሽልማት ይሰጥ አይሰጥ ግን አልታወቀም።