ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቶማስ ሳንካራ ግድያ በቀድሞው የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝደንት ላይ የ30 ዓመት እስር ተጠየቀ
በቀድሞ በቡርኪና ፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራ ግድያ ተባባሪ ናቸው የተባሉት የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ብሌስ ኮምፓዎሬ ላይ የ30 ዓመት የእስር ቅጣት ተጠየቀባቸው።
የቡርኪና ፋሶ ዐቃቤ ሕግ የቀድሞው ፕሬዝደንት በለውጥ ሃዋሪያው ቶማስ ሳንካራ ግድያ ተሳታፊ በመሆናቸው የሦስት አስርት ዓመታት እስር ሊበየንባቸው ይገባል ብሏል።
ቶማሳ ሳንካራ እአአ 1987 ላይ መገደላቸው ይታወሳል። የፈረንሳይ መንግሥት የቶማስ ሳንካራን ግድያ የሚመለከት ዝርዝር የጦር ሠራዊት ሰነድ ይፋ ለማድረግ መስማማቱን ተከትሎ በቀድሞው መሪ ግድያ ዙሪያ ባለፈው ዓመት ምርመራ መጀመሩ ይታወሳል።
የቀድሞ የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝደንት ቶማስ ሳንካራ በአገሪቱ መዲና ዋጋዱጉ ውስጥ በ37 ዓመታቸው ከተገደሉ በኋላ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል።
ይህንንም ተከትሎ በዚያው ዓመት ብሌስ ኮምፓዎሬ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን መጥተዋል።
ፕሬዝደንት ኮምፓዎሬ በሕዝባዊ አመጽ ከመንበራቸው እስተወገዱበት እአአ 2014 ድረስ ለ27 ዓመታት ቡርኪና ፋሶን መርተዋል።
ኮምፓዎሬ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ከአገር ተሰደው መኖሪያቸውን በጎረቤት አገር አይቮሪ ኮስት አድርገዋል።
ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው የጦር ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝደንት በሌሉበት "በአገር ደኅንነት ላይ ጥቃት በማድረስ" ወንጀል ጥፋተኛ እንዲላቸው ጠይቋል።
ከዚህ በተጨማሪም የቶማስ ሳንካራ እና 12 የሳንካራ ባልደረቦች ግድያን በማቀነባበር ኮምፓዎሬ እንዲጠየቁ ከሳሾች ጠይቀዋል።
የቀድሞ ፕሬዝደንት የሳንካራ የቅርብ ወዳጅ የነበሩ ሲሆን በሳንካራ ግድያ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የለኝም ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ቶማስ ሳንካራን የገደለ የኮማንዶ ቡድን መርተዋል የተባሉት ሃይሲንዝ ካዳንዶ በ30 ዓመት እስር እንዲቀጡ እና ቶማስ ሳንካራ ከሥልጣን ባስወገደው መፈንቅለ መንግሥት ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ የተባሉት ጊልበርት ዲኤንዴሬ በ20 ዓመት እንዲቀጡ ጠይቋል።
ጊልበርት ዲኤንዴሬ እአአ 2015 ላይ በተፈጸም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጥፋተኛ ተብለው የ20 ዓመት እስር ተበይኖባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በቶማስ ሳንካራ ጉዳይ በአካል ከችሎት ፊት ቀርበዋል።