ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ በሱዳን ጥያቄ ከአቢዬ ሊወጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, UNISFA
አቢዬ ግዛት በተባባሩት መንግሥታት ጥላ ስር በሰላም አስከባሪነት ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያ ወታደሮችን ለማስወጣት የሱዳን መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ከስምምነት መድረሳቸው ተዘገበ።
የሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ሱና እንደዘገበው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል-ሳዲቅ አል-መሐዲ ከተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣናት ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቀጣይ ሦስት ወራት ከአቢዬ እንዲወጡ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ሠራዊቷን ከሱዳን ድንበር ማንቀሳቀሷን ተከትሎ ሱዳን በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር የነበሩ ቦታዎችን ከያዘች በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል አለምግባባት መከሰቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ከወራት በፊት የሱዳን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት "የኢትዮጵያ ሠራዊት በምሥራቃዊ የሱዳን ድንበር አካባቢ እየተጠናከረ ባለበት ጊዜ ስትራተጂክ በሆነው የሱዳን ማዕከላዊ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ ኃይሎች እንዲኖሩ መፍቀድ ምክንያታዊ አይሆንም" በማለት የመንግሥታቱ ድርጅት በስሩ ያሉትን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን እንዲያስወጣ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ፓራፊት ኦናንጋ-አንያንጋ እና ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተሳተፉበት በኢንተርኔት በተደረገ ውይይት በሱዳን ጥያቄ መሠረት ኢትዮጵያውያኑ ወታደሮች እንዲወጡ ከስምምነት መደረሱን ሱና ዘግቧል።
በዚህም መሠረት የመንግሥታቱ ድርጅት በአቢዬ ግዛት ባሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ አባል የሆኑት ከሦስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮችና የፖሊስ አባልት በሱዳን ጥያቄ መሰረት በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ከሱዳን ይወጣሉ ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ጨምረውም መንግሥታቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባልት ከአቢዬ ግዛት በተሳካ ሁኔታ እንዲወጡና የሌላ አገር ኃይሎች እንዲተኳቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ ትብብር እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
በምህጻረ ቃል ዩኒስፋ በመባል የሚታወቀው ሰላማ አስከባሪ ኃይል ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ባወዛገበችው በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው የአቢዬ ግዛት ነው የተሰማራው።
ደቡብ ሱዳን ነጻ አገር መሆን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ከተለያዩ አገራት የተወጣታ ኃይል በስፍራው ተሰማርቷል።
በአቢዬ ግዛት የመንግሥታቱ ድርጅት ያሰማራቸው ሰላም አስከባሪዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኢትዮጰጵያ ሠራዊት ነው።
በዚህ ኃይል ውስጥ በአጠቃላይ 4,190 ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ሰላም አስከባሪዎች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 3,158 ወታደሮችና ሰባት የፖሊስ መኮንኖች ከኢትዮጵያ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።














