ከጋና ወደ አሜሪካ በሚበር አውሮፕላን ውስጥ የወለደችው እናት አድናቆት ተቸራት

ታትሟል

አንዲት ነፍሰ ጡር ከጋና ወደ አሜሪካ በሚደረግ በረራ ላይ በድንገት በመውለዷ ተሳፋሪዎች ድንጋጤና አድናቆትን አስተናግደዋል።

ራሷን ጂጂ እያለች የምትጠራው ይህች እናት ከመውለጃዋ ቀናት በፊት በድንገት ነው በረራ ላይ ሳለች የወለደችው።

በበረራው መሀል የነበረ አንድ ሐኪም የቢዝነስ በረራ ክፍሉን በፍጥነት ወደ ጊዜያዊ የማዋለጃ ክፍል በመቀየር ጂጂ ልጇን በሰላም እንድትገላገል እርዳታ አድርጓል።

ጂጂ ልጅ የመውለጃ ጊዜዋ እንዲሆን ትጠብቅ የነበረው በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ጋዜጠኛ ናንሲ አዶቢያ ከአክራ ወደ አሜሪካ በነበረው በረራ ውስጥ ነበረች።

ናንሲ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ብዙዎቹ ተሳፋሪዎች ‹ከተሳፋሪ መካከል ሐኪም አለ ወይ?› የሚለው ጥያቄን የሰሙ ቢሆንም ለምን ይህ ጥያቄ እንደተጠየቀ ግን መረጃው አልነበራቸውም።

ጥሪውን ተከትሎ ዶ/ር ስቴፈን የተባሉ ሐኪም ጂጂን በቀላሉ እንድትገላገል እርዳታ አድርገውላታል።

ዶ/ር ስቴፈን ስለሁኔታው ሲናገሩ፣ "ጥሪውን ተከትሎ እኔ፣ አንዲት ነርስና ሌሎች የበረራ አስተናጋጆች በጋራ ጂጂ በሰላም እንድትገላገል ለመርዳት ችለናል" ብለዋል።

ጂጂ ልጇን በበረራ ላይ ሳለች ለመገላገል የወሰደባት ጊዜ 45 ደቂቃ ብቻ ነው።

ከዚያ በኋላ የተከተለው የተወለደው ልጅ ለቅሶ ነው።

አውሮፕላኑ ዋሺንግተን ሲደርስ ለአራሷና ለልጁ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ተደርጎላቸዋል።

ነፍሰ ጡሮች በረራ ላይ ባለ አውሮፕላን ውስጥ ሲገላገሉ ይህ የመጀመርያው አይደለም።

ሆኖም ግን ከስንት አንድ የሚያጋጥም ክስተት ነው።

ባለፈው ጥር ከኳታር ወደ ኡጋንዳ በነበረ አንድ በረራ ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞ ከተሳፋሪዎች መሀል የነበረች አንዲት ካናዳዊት ሐኪም እርዳታ ልጅ ለመውለድ በቅታለች።

በዩኬ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት መሠረት ከ27 ሳምንታት እርግዝና በኋላ ምጥ በማንኛውም ሰዓት ሊፋፋም ስለሚችል በርካታ አየር መንገዶች ሆዷ የገፋ ነፍሰ ጡርን ለማሳፈር ፍቃደኛ አይሆኑም።