የቡርኪና ፋሶው ጄኔራል ፕሬዝዳንቱን ከገለበጡ በኋላ የመጀመሪያውን ንግግር አደረጉ

ሉቴናንት ኮሎኔል ፖል-ሄንሪ ዳሚባ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የቡርኪና ፋሶ አዲሱ ወታደራዊ አገዛዝ መሪ "ሁኔታዎች ሲመቻቹ" አገሪቱ ወደ ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር ትመለሳለች ብለዋል።

ሉቴናንት ኮሎኔል ፖል-ሄንሪ ዳሚባ ሰኞ ዕለት ፕሬዝደንት ሮች ካቦሬን ከሥልጣናቸው መፈንገላቸው ይታወሳል።

ኮሎኔሉ፤ ፕሬዝደንቱ በኢስላማዊ ታጣቂዎች የሚነሱ ግጭቶችን ማስቆም አልቻሉም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ቀይ ባርኔጣና ወታደራዊ መለዮ ታጥቀው በብሔራዊ ቴሌቪዥን የታዩት ሉቴናንት ኮሎኔል ዳሚባ ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ አደባባይ ሲወጡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

"ሁኔታዎች ሲስተካከሉ፤ ሕዝባችን በሚሰጡት ቀነ ገደብ መሠረት ነገሮች ወደ ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር እንደሚመለሱ ቃል እገባለሁ" ብለዋል።

የ41 ዓመቱ ሉቴናንት ኮሎኔል ለለውጥ የሚረዳ ፍኖተ ካርታ ለመቅረፅ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩም ገልጠዋል።

ኮሎኔሉ አክለው ቡርኪና ፋሶ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፍ አጋሮች ያስፈልጓታል ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በቡርኪና ፋሶ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት መቃወሙ የሚታወስ ነው።

"ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አገራችንን እንዲያግዝና ከዚህ መከራ እንድንወጣ እንዲያደርግ ጥሪ አቀርባለሁ።"

የቡርኪና ፋሶ መከላከያ ሠራዊት የሲቪሉን ሥልጣን መጨበጡን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ያወጀው ባለፈው ሰኞ ነበር።

በወቅቱ አንድ ወታደራዊ መኮንን መፈንቅለ መንግሥቱ ያስፈለገው በአገሪቱ እየታየ ያለውን የደኅንነት ስጋት ከግምት በማስገባት ነው ብለው ነበር።

ፕሬዝደንት ካቦሬ ከኢስላማዊ ታጣቂዎች የሚሰነዘረውን ጥቃት መመከት ባለመቻላቸው ወቀሳ ሲቀርብባቸው ነበር።

ሉቴንናት ኮሎኔል ዳሚባ ከኢስላማዊ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ጦርነት ቀዳሚ ሚና የነበራቸው ሰው ናቸው።

ኮሎኔሉ ባለፈው ዓመት ይህንን ጦርነት በማስመልከት አንድ መጽሐፍ ጽፈው ነበር።

በተመሳሳይ ኢስላማዊ ታጣቂዎችን ለመመከት በሚል ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የቡርኪና ጎረቤት በሆነችው ማሊ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ የሚዘነጋ አይደለም።

ቡርኪና ፋሶ በቅርብ ዓመታት መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባት ሦ ስተኛዋ ምዕራብ አፍሪካዊት አገር ናት።

ጊኒና ማሊ መፈንቅለ መንግሥት ስለተካሄደባቸው ኤኮዋስ የተሰኘው ቀጣናዊ ማዕቀፍ ወደ ሲቪል አገዛዝ እንዲመለሱ በማለት ቅጣት ጥሎባቸዋል።

ኤኮዋስ ዛሬ አርብ ተሰብስቦ በቡርኪና ፋሶ ጉዳይ ይመክራል።