ኩርድ መራሹ ሃይል በአይኤስ ተይዞ የቆየውን እስር ቤት መቆጣጠሩን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Farhad Shami
በኩርድ ሃይሎች የሚመራው የሚሊሺያ ጥምረት በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የሚገኘውን እና ራሱን የእስላማዊ መንግስት (አይ ኤስ) ብሎ በሚጠራው ቡድን ከስድስት ቀናት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለውን እስር ቤት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ገለፀ።
በአሜሪካ የሚደገፈው የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ሃይል (ኤስዲኤፍ) ቃል አቀባይ በትዊተር ገፃቸው እንዳስታወቁት በሃሳካ ግዋይራን እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሁሉም "የዳኢሽ አሸባሪዎች" እጃቸውን ሰጥተዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እስረኞችም በእስር ቤቱ ውስጥ እንደነበሩም ተዘግቧል።
አይ ኤስ ባለፈው ሃሙስ የጅምላ ጥቃት መሰንዘር ከሞከረ በኋላ በተነሳ ግጭት ቢያንስ 181 ሰዎች ህይወት ማለፉ ሲዘገብ ከእነዚህ ውስጥም 124ቱ ታጣቂዎች እና እስረኞች ሲሆኑ 50 ፖሊሶች እንዲሁም የኤስዲኤፍ ተዋጊዎች እና የእስር ቤት ጠባቂዎች እንደሚገኙበት የሶሪያ የሰብአዊ መብት ኦብሰርቫቶሪ የተሰኘው ተቋም አስታውቋል።
ኤስዲኤፍ ከአይ ኤስ ጋር ባደረገው ጦርነት ምክንያት 12 ሺህ አዋቂ ወንዶች እና ታዳጊ ወንድ ልጆች በሶሪያ ሰሜንና ምስራቃዊ አካባቢዎች በሚገኙ የተጨናነቁ ጊዜያዊ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።
እንዲሁም 60 ሺህ አዋቂ ሴቶች፣ ልጃገረዶች እና ወጣት ወንዶች ልጆች በካምፖች ውስጥ ታጉረዋል።
አይ ኤስ በጓዋይራን እስር ቤት ላይ ሃሙስ ምሽት ላይ የሰነዘረው ጥቃት እኤአ በ2019 ከፍተኛ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ ያደረገው ትልቁ ወታደራዊ ኦፕሬሽን መሆኑም ታውቋል።
ቁጥራቸው ወደ 4000 ገደማ ከሚሆኑ እስረኞች ውስጥ የቡድኑን አባላት ለማስለቀቀ የተለያዩ ስልቶችን መጠቀሙም ታውቋል።
እስር ቤቱን መልሶ ለመቆጣጠርም በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤስዲኤፍ ተዋጊዎች እና አጋር የሆኑት የአሳይሽ የጸጥታ ሃይል አባላት በተዋጊ ጄቶች፣ ሄሊኮፕተሮች እና በታጠቁ ተሽከርካሪዎች ታግዘው እስር ቤቱን ለማስለቀቅ ተዋግተዋል።
ኤስዲኤፍ እንደገለጸው ታግተው የነበሩ 23 የእስር ቤት ጠባቂዎች የተለቀቁ ሲሆን ከ1,000 በላይ ታጣቂዎች እና እስረኞች እጃቸውን መሰጠታቸውን ቃል አቀባዩ ፋርሃድ ሻሚ ረቡዕ ከሰአት በኋላ የኦፕሬሽኑን መጠናቀቅ በገለጹበት ወቅት አስታውቀዋል።
ሚስተር ሻሚ ኤስዲኤፍ የአይ ኤስ ታጣቂዎች እና እስረኞች እንደ ሰው ምሽግ ተጠቅመውባቸወዋል ያሏቸውን የ700 ህጻናት ጉዳይ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ ያሉት ነገር የለም።
ነገር ግን "የልጆቹ ደህንነት ዋና ጉዳይ ባይሆን ኖሮ ይህንን ኦፕሬሽን ከአንድ እስከ ሁለት ቀን በከባድ መሳሪያ ልናጠናቅቀው እንችል ነበር" ሲሉ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ጉዳዮችን የሚያስተባብረው ዩኒሴፍ ማክሰኞ ምሽት እንዳስታወቀው በእስር ቤቱ ውስጥ የነበሩ ሕጻናትን በተመለከተ "እጅግ አሳሳቢ የሆነ የህጻናቱ የሞት ቁጥርየሚያሳዩ ሪፖርቶች" እንደደረሱት እና ሁሉም ተዋጊ ወገኖች ህጻናቱ በሰላም ለቀው እንዲወጡ እንዲፈቅዱላቸው ጠይቀው ነበር።












