አሜሪካ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ለግብፅ ልትሸጥ ነው

ወታደራዊ አውሮፕላኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለግብፅ የወታደራዊ መጓጓዣ አውሮፕላኖች ሽያጭ እንዲፈጸም ፈቀደ።

ግብፅ ከአሜሪካ ለመግዛት ጥያቄ ያቀረበችው 12 ወታደራዊ ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ሲሆን ዋጋቸውም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የአየር መከላከያ የራዳር ሥርዓቶችና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለግብፅ ሸጣለች።

ይህ የወታደራዊ መገልገያዎች ሽያጭ የአሜሪካ መንግሥት ለግብፅ የፈቀደው፣ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በግብፅ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ በቅርቡ ትችት ካቀረበ በኋላ መሆኑ በአንዳንዶች ዘንድ ጥያቄን ፈጥሯል።

ባለፈው መስከረም ወር ላይ በአገሪቱ ካለው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጋር በተገናኘ የአሜሪካ መንግሥት ለግብፅ ተመድቦ የነበረን የ130 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያዝ መወሰኑ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣንት ለዚህ ውሳኔያቸው እንደምክንያት አቅርበውት የነበረው ግብፅ በአገሯ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሻሻል ሳትችል በመቅረቷ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ገብፅ በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ የአሜሪካ ወዳጆች መካከል በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሲሆን፣ በየዓመቱም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወታደራዊ ድጋፍን ከአሜሪካ ታገኛለች።

በአገሪቱ ውስጥ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ ወደ መሪነት መንበር የመጡት የቀድሞው ጄነራል የፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲሰ መንግሥት በተደጋጋሚ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲወቀስ ቆይቷል።

አሜሪካንም በአገሪቱ ያለው የመብት ጥሰት እንዲስተካከል ስትጠይቅና ግፊት ስታዳርግ ቆይታ፣ በዚህ ሳቢያ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ለጊዜው ማገዷን አሳውቃ ነበር።

ግብፅ በአካባቢው ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን በየጊዜው ሠራዊቷን ለማዘመን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

ከወታደራዊና ከፀጥታ አንጻር ግብፅ በጎረቤት ሊቢያ የምትደግፈውን ቡድን ወደ ሥልጣን ለማምጣት ድጋፍ እያደረገች ሲሆን ከሱዳን ጋር ደግሞ ሞቅ ቀዝቀዝ የሚል የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አለባት።

ከዚህ ባሻገር ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር ባትጋራም ግንባታው ወደ መጠናቀቁ በተቃረበው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ላለፉት አስር ዓመታት ውዝግብ ውስጥ ቆይታለች።