በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው እግር ኳስ ተጫዋች ሮቢንሆ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ሆነ

ሮቢንሆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ብራዚላዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ሮቢንሆ እ.ኤ.አ. በ 2013 በሚላን ከተማ በቡድን በተፈጸመ የመድፈር ወንጀል የቀረበበትን ፍርድ ለመጨረሻ ግዜ ይገባኝ ቢልም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የታችኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ አደረገ።

ትላንት ረቡዕ የተሰየመው የሮም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ 37 ዓመቱን ኳስ ተጨዋች ተፈርዶበት የነበረውን የዘጠኝ ዓመት እስራት አጽንቷል።

እ.ኤ.አ. በ 2017 ሮቢንሆ እና ሌሎች አምስት ብራዚላውያን የ22 ዓመቷን አልባኒያዊ ሴት በምሽት ክበብ ውስጥ የጾታዊ ጥቃት በማድረስ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት።

ከዚህ ቀደም በታህሳስ 2020 ይግባኝ በውሳኔው ላይ ይግባኝ ቢቀርብበትም ይግባኙ ውድቅ ተደርጎ ነበር። ሮቢንሆ የሚኖርበት ብራዚል በሕገ መንግስት ደረጃ መንግስት ዜጎቹን ለሌላ አገር አሳልፎ እንዳይሰጥ የሚከለክል መሆኑን ተከትሎ ቅጣቱን ይፈጽማል የሚል ግምት ባይኖርም ጣሊያን ደቡብ አሜሪካዊቷን አገር ቅጣቱን በአገሩ ውስጥ እንዲፈጽም መጠየቅ ትችላለች።

ለብራዚል 100 ጊዜ የተጫወተው ሮቢንሆ በ2005 ኑሮውን ወደ ሪያል ማድሪድ ከማዛዋሩ የእግር ኳስ ህይወቱን በሳንቶስ ነበር የጀመረው።

በአራት የውድድር ዘመናት ሁለት የላሊጋ ዋንጫዎችን አንስቷል። እ.ኤ.አ. በ 2008 ማንቸስተር ሲቲን ሲቀላቀል በወቅቱ የእግሊዝ ከፍተኛው ክፍያ 32.5m ፓውንድ ተከፍሎት ነበር።

ነገር ግን በእንግሊዝ ቆይታው ውጤታማ ለመሆን ባለመቻሉ በጥር 2010 ለሳንቶስ በውሰት ተሰጥቷል። በኤስ ሚላን ቆይታው ሴሪአን አሸንፏል። በቻይና እና በቱርክ ላሉ ክለቦች ከተጫወተ በኋላ 2020 በአምስት ወር ኮንትራት ወደ ሳንቶስ ቢመለስም ፊርማው ከፍተኛ ትችት ማጋጠሙን ተከትሎ የብራዚሉ ክለብ ኮንትራቱን አቋርጦ "ተጫዋቹ በጣሊያን እየተካሄደ ባለው ጉዳይ በመከላከሉ ላይ ብቻ እንዲያተኩር" ስል ውሉን አቋርጫለሁ ሲል አስታወቆ ነበር።