የዩኬ ጠ/ሚ ባልደረቦች የኮቪድ ክልከላዎችን ተላልፈው ተጨማሪ ድግሶችን አዘጋጅተው ነበር ተባለ

ታትሟል

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የቦሪስ ጆንሰን ጽ/ቤት ሠራተኞች የኮቪድ-19 ገደብን ተላልፈው የመጠጥ ድግስ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅተው ነበር ተባለ።

በዩኬ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተጥሎ የነበረው ሕግ ጥስው በመጠጥ ድግስ ላይ ተገኝተው ቁጣ የበረታባቸው የቦሪስ ጆንሰን ሠራተኞች ተጨማሪ ሕግን የሚጥሱ ፕሮግራሞች አዘጋጅተዋል የሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው ነው።

ነምበር ቴን እየተባለ የሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ከኤድንብራው መስፍን የቀብር ሥነ ሥርዓት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኮቪድ ገደቦችን ተላልፈው ሁለት የሽኝት ፕሮግራሞችን አዘጋጅተው እንደነበር ነው ዘ ቴሌ ግራፍ የዘገበው።

እንደ ዘ ቴሌግራፍ ዘገባ ከሆነ ፕሮግራሞቹ እስከ 30 የሚጠጉ ሰዎች ያካተተ ሲሆን የአልኮል መጠጥ እና ጭፈራ ነበረባቸው።

ሠራተኞቹ ይህን በሚያደርጉበት ወቅት የተለያዩ ቤት የሚኖሩ ሰዎች አንድ ቤት ውስጥ መገኘት የማይችሉበት ወቅት ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት በሚያዚያ ወር የተደረጉትን ፕርግራሞች ጽህፈት ቤቱ አላስተባበለም።

የቦሪስ ጆንሰን የቀድሞ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጄምስ ስላክ ከጽህፈት ቤቱ ወጥቶ ዘ ሰን ጋዜጣ ላይ ሥራ ያገኘው ባለደራባቸው ሲሸኝ "የመሰናበቻ ንግግር ማድረጋቸውን" አረጋግጠዋል።

በወቅቱ ከከተማ ውጪ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሪስ ቦንሰን ግን ፕሮግራሙ ላይ አልታደሙም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው ውስጥ ገደቦችን ተላለፈው መጠጥ ያለበት ፕርግራም ላይ በመታደማቸው ከራሳቸው ፓርቲ ቁጣ ተሰንዝሮባቸዋል።

ፕሮግራሞቹ የተካሄዱት ዩናይትድ ኪንግደም የልዑል ፊሊፕ ሞትን ተከትሎ ለቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን ባወጀችበት ወቅት ነበር።

ፕርግራሞቹ ሲከናወኑ በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መሰባሰብ የታገደበት ወቅት ሲሆን ተሳታፊዎቹ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በመጠጥ እና በዳንስ አሳልፈዋል።

ይህ ዜና የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣውን ደንብ ተላልፈው አንድ ፕርግራም ላይ መሳተፋቸው ተሰምቶ ቁጣን ከቀሰቀሰ በኋላ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዕረቡ ለዚህ ድርጊታቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።