የኬንያ ፖሊስ ሕገ-ወጥ ያላቸውን 91 ኢትዮጵያውያንን ከአንድ ቤት ያዘ

የፎቶው ባለመብት, Huw Evans picture agency
የኬንያ ፖሊስ በአገሪቱ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ተገኝተዋል ያላቸውን ከ90 በላይ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ።
ፖሊስ ከጎረቤት አገራት በሕገ-ወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን ለመቆጣጠር እሁድ ምሽት አካሄድኩ ባለው አሰሳ 91 ኢትዮጵያውያን ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ መያዙን ገልጿል።
የአገሪቱ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል እንዳለው ሁሉም ስደተኞች ወንዶች ሲሆኑ እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ነው። ጨምሮም እንዲቆዩ ከተደረጉበት ቤት ሰብረው ለመውጣት ሙከራ አድርገው እንደነበረም አመልክቷል።
በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት በጭነት መኪና ወደ ኬንያ መግባታቸውን ያመለከተው ፖሊስ፤ በተያዙበት ቤት ውስጥ በጊዜያዊነት ቆይተው ወደ ሌላ አገር ሊሸጋገሩ እንደነበር ተገልጿል።
ስደተኞቹን የሚያጓጉዙት ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የገቡትን ከ90 በላይ ኢትዮጵያውንን በአንድ ቤት ያቆይዋቸው ቀጣይ ጉዟቸውን አስኪያመቻቹ ድረስ እንደሆነ ፖሊስ ተናግሯል።
አሁን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ገብተው የተያዙት ስደተኞች በቁጥር ከፍተኛ ተብሎ ከሚጠቀሱት መካከል ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኑን ያመጧቸው የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ ይገኛል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በተመሳሳይ በሕገ-ወጥ መንግድ ወደ ኬንያ ገብተው ተገኝተዋል ያላቸውን አራት አዋቂዎችና 10 ልጆችን በአጠቃላይ 14 ኢትዮጵያውያንን ፖሊስ በቁጥጥር ማዋሉን አስታውቋል።
ስደተኞቹ ሊያዙ የቻሉት ማዕከላዊ ኬንያ ውስጥ የተከሰተን አደጋ ተከትሎ ሲሆን በተደረገ ፍተሻ ኬንያ ውስጥ ለመገኘት የሚያስችል ሕጋዊ ሰነድ እንደሌላቸው በመታወቁ ነበር የተያዙት።
አስራ አራቱን ኢትዮጵያውያን ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዙ ነበር የተባሉ ሁለት ኬንያውያንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሌሎች አገራት ለመሸጋገር በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም ፖሊስ ባካሄዳቸው አሰሳዎችና ክትትሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል።












