በሱዳን በቀጠለው ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ለጉዳት ተዳረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሱዳን መዲና ካርቱም ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የተደረገውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም እሁድ እለት በተደረጉ ሰልፎች ሁለት ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን ሐኪሞች አስታወቁ።
ሐኪሞቹ እንዳሉት አንደኛው ግለሰብ በአስለቃሽ ጭስ መያዣ ጭንቅላቱ ተመትቶ በአንጎሉ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፤ ሌላኛው ግለሰብም በአስለቃሽ ጭሱ መያዣ አንገቱ ላይ ተመትቶ ለሞት ተዳርጓል።
ከተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ያለውና 'ሴንትራል ዶክተርስ ኮሚቴ' በመባል የሚጠራው የሐኪሞች ቡድን ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ እስካሁን ድረስ 63 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች እርምጃ ተገድለዋል ብሏል።
የሱዳን ፖሊስ በበኩሉ እሁድ ዕለት በተፈጠረው አለመረጋጋት 86 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል።
የሱዳን የዜና ወኪል ለእስር የተዳረጉትን ግለሰቦች "ሥርዓት የሌላቸው ተቃዋሚዎች" ሲል ገልጿቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በአገሪቷ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታትና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር ለማገዝ ከሱዳን መሪዎች ጋር ንግግር ለመጀመር እየሞከርኩ ነው ብሏል።
ከሳምንት በፊት አብደላ ሐምዶክ በወታደራዊ ኃይሉና በዴሞክራሲ አቀንቃኞች መካከል ያለው ውጥረት በቀጠለበት ወቅት ከሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በፈቃዳቸው ለቀዋል።
ተቃዋሚዎች በጄነራል አል ቡርሐርን የሚመራው የሱዳን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ እና ጦር ሠራዊቱ ከአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እጁን እንዲያወጣ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ሰላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሱዳንን የመሩት አልበሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ተወግደው እስር ቤት ከገቡ በኋላ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመምራት የሽግግር መንግሥት ቢቋቋምም፣ በወታደራዊና በሲቪል መሪዎች መካከል መግባባት ሳይፈጠር እስካሁን ቆይቷል።
ጥቅምት ወር ላይ በጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ደግሞ በአገሪቱ ያለውን ቀውስ አባብሶታል።












