የኒጀር ፖሊስ በከንቲባው መኪና ሲጓጓዝ የነበረ 200 ኪሎ ግራም ኮኬይን ያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኒጀር አንድ ከንቲባ እና አሸከርካሪያቸው ከ200 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮኬይን በመኪናቸው ውስጥ እንደያዙ በሰሜን ኒጀር በሚገኝ በረሃ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
በስም ያልተጠቀሱት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች እፁ ከማሊ ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ሊቢያ ሲያጓጉዙ ነበር ተብሏል።
የኒጀር የአደንዛዥ እፅ ፖሊስ ኤጀንሲ እንዳለው ኮኬይኑ እስካሁን በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ከተያዘው የኮኬይን እፅ መጠን ይህ ከፍተኛው ነው።
በአካባቢው እፅ ማዘዋወርና በፖሊስ መያዝ የተለመደ ሆኗል።
ረቡዕ እለት የኒጀር የሕገ ወጥ እፅ አዘዋዋሪ ማዕከላዊ መሥሪያ ቤት፣ ፖሊስ ከፍተኛ መጠን ያለውን ይህን ኮኬይን በአገሪቷ በኩል ወደ ሊቢያ ሲዘዋወር እንደነበር እንደሚያውቅና ዱካውን ሲከታተል ቆይቷል ብሏል።
በዚህም መሠረት ከአራት ቀናት በፊት በአጠቃላይ 214 ኪሎግራም የሚመዝኑ199 የኮኬይን ጡቦች የፋቺ ከንቲባ ቢሮ በሆነ ተሽከርካሪ ውስጥ መያዙን የሕገ ወጥ እፅ አዘዋዋሪ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ናና አይቻቱ ኡስማን ባኮ አስረድተዋል።
ተሽከርካሪው እሁድ እለት በፖሊስ ሲያዝ ከፋቺ ተነስቶ ወደ ሊቢያ ዲርኮ ከተማ ሲያመራ ነበር።
"አገራችንን ይህንን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ኮኬይን ስትይዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው" ብለዋል ቃል አቀባዩ ባኮ።
ቃል አቀባዩ አክለውም እፁ ወደ አውሮፓ እያመራ የነበረ ሲሆን በጎዳና ላይ ዋጋ በግምት19 ሚሊየን ዶላር እንደሚያወጣ ገልጸዋል።
ከንቲባውና ሹፌሩ ወደ ኒጀር ዋና መዲና ኒያሚ ለጥያቄ ተወስደዋል።
ፋቺ ከሰሜናዊ አጋዴዝ ከተማ 400 ኪሎ ሜትር ገደማ የምትርቅ እና በቴነር በረሃ የባህር ዳርቻ የምትገኝ ከተማ ናት። በቴምርና በጨው ንግድ ማዕከልነቷም ትታወቃለች።
አካባቢውን በደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ መካከል እፅ ለማዘዋወርና ለስደተኞች ዝውውር እንዲሁም ለተለያዩ መሠል ሕገ ወጥ ዝውውሮች እንደ መንገድ ይጠቀሙበታል።












