የሜዳ ቴኒስ ኮከቡ ኖቫክ ጆኮቪች አውስትራሊያ እንዳይገባ ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሜዳ ቴኒስ ኮከቡ ኖቫክ ጆኮቪች ወደ አውስትራሊያ ሊገባ ያደረገው መኩራ ሜልቦርን ከደረሰ በኋላ በተፈጠረ ግርግር ምክንያት ከሽፎበታል።
የዓለም ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ጆኮቪች በከተማዋ አየር ማረፊያ ለሰዓታት ከተንገላታ በኋላ ወደ አውስትራሊያ ለመግባት የሚስችለውን ቅደመ ሁኔታ አሏማላም ተብሎ ወደመጣበት እንዲመለስ ታዟል።
ጆኮቪች በተደጋጋሚ መንግሥት ወዳሰናዳው ማቆያ ሆቴል እየገባ እየወጣ ሂደቱን በመከታተል ላይ ይገኛል።
ይህ የኮከቡና የአውስትራሊያ መንግሥት ግርግር ዜና የተሰማው ጆኮቪች አውስትራሊያ ኦፕን በተሰኘው ውድድር ላይ ሊሳተፍ ባቀደበት ወቅት ነው።
ጆኮቪች ወደ ሜልቦርን እንዳይገባ የተከለከለው ምናልባት ክትባት ስላልወሰደ ነው የሚሉ መላ ምቶች እየተሰሙ ነው።
ምንም እንኳ የሜ ዳቴኒስ ተጫዋቹ ይከተብ አይከተብ ይፋ ባያደርግም የክትባቱ ደጋፊ እንዳልሆነ ባለፈው ዓመት ጠቆም አድርጎ ነበር።
ቴኒስ አውስትራሊያ እንዳለው ችግሩ የተፈጠረው ጆኮቪች ረቡዕ ዕለት ከዱባይ በመጣበት ወቅት ነው።
የአውስትራሊያ ድንበር ጥበቃ ባወጣው መግለጫ "ጆኪቪች ወደ አውስትራሊያ ለመግባት የሚያስችለውን ቅደመ ሁኔታ አሏማላም፤ በዚህም ምክንያት ቪዛው ተሰርዞበታል" ብሏል።
"ትክክለኛ ቪዛ ያልያዙ አሊያም ቪዛቸው የተሰረዘባቸው የአውስትራሊያ ዜጎች ያልሆኑ ሰዎች በቁጥጥራችን ሥር ውለው ከአውስትራሊያ ይወገዳሉ" ይላል መግለጫው አክሎ።
የቪክቶሪያ ግዛት ጊዜያዊ ስፖርት ሚኒስትር ግዛታቸው በጆኮቪች የቪዛ ሂደት ጣልቃ እንደማትገባ አስታውቀዋል።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ጆኮቪች ተነጥሎ በደል ደርሶበታል መባሉን አጣጥለው ማንም ከሃገሪቱ ሕግ በላይ አይደለም ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሞሪሰን ለጆኮቪች የተለየ የሕክምና ይለፍ እንዳልተሰጠውና የቀረበው ማስረጃ በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጆኪቪች ጉዳዩን በሕግ ይዞት አሊያም ድጋሚ ለቪዛ አመልክቶ ሊገባ እንደሚችል ዘግበዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ደግሞ ተጫዋቹ ከአየር ማረፊያው ሜልቦርን ወደሚገኝ ከዚህ በፊት የኮቪድ-19 ማገገሚያ ሆኖ ሲያገለግል ወደነበር ማቆያ ተወስዶ ነበር ሲል ፅፏል።
የአውስትራሊያ ጤና ሚኒስትር ጆኮቪች ላይ የደረሰው "ቆራጥ" ውሳኔ ቢሆንም "ትክክል" ነበር ሲሉ ሞግተዋል።
የቴኒስ ኮከብ አውስትራሊያ ውስጥ መንገላታት የሃገሩ ሰርቢያ ልጆችን አስቆጥቷል። አባቱ ስርጃን ጆኮቪች ልጃቸው አየር ማረፊያ ውስጥ በፖሊስ ተከቦ እንዳለ ተናግረው ነበር።
ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ቩቺች ኮከቡ "የጥቃት ሰለባ" ሆኗል ብለው ሁሉም ሰርቢያዊ ከተጫዋቹ ጀርባ እንደሆነ ተናግረዋል።
አውስትራሊያ ጥብቅ በሆነው የኮቪድ-19 ደንብ ትታወቃለች።
ከሃገሪቱ ሕዝብ 90 በመቶ ከ16 ዓመት በላይ ያሉ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ተከትበዋል። እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ሰዎች ከግዛት ግዛትም ሆነ ከሃገር ውጭ መብረር አይችሉም።
በርካታ አውስትራሊያውያን ከዚህ በፊት መንግሥት ታዋቂና ሃብታም ሰዎች እንደልብ እንዲገቡ እንዲወጡ እየፈቀደ ነው ሲሉ ወቀሳ ያሰሙ ነበር።
ጆኮቪች ዘጠኝ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳው የአውስትራሊያ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ውድድር በፈረንጆቹ ጥር 17 በሜልቦርን አዘጋጅነት ይጀመራል።












