ቴክኖሎጂ፡ ዴንማርክ በዓለም የመጀመርያውን ኃይል አመንጪ ሰው ሠራሽ ደሴት ልትገነባ ነው

የፎቶው ባለመብት, DANISH ENERGY AGENCY
ዴንማርክ በዓለም የመጀመርያ ነው የተባለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በሰው ሠራሽ ደሴት ላይ ልትገነባ እንደሆነ ተገለጸ።
በደሴቱ የሚገነባው ታዳሽ የኃይል ማመንጫ በግዝፈቱ ወደር የለውም ተብሏል። ግንባታው ሲጠናቀቅም ለ3 ሚሊዮን ቤተሰቦች የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል።
በዓለም እስከዛሬ ራሱን የቻለ የኃይል ማመንጫ ሰው ሠራሽ ደሴት ተገንብቶ አያውቅም። ይህ በዴንማርክ ባሕር ላይ የሚገነባው ማመንጫ በግዝፈቱም አነጋጋሪ ሆኗል።
ሠው ሰራሽ የኃይል ማመንጫ ደሴቱ 120ሺህ ስኩዌር ሜትር ይሰፋል። ይህም በግምት 18 የእግር ኳስ ሜዳዎች ተቀጣጥለው የሚኖራቸው ስፋት ያህል ነው።
ሆኖም ሁኔታዎች ከተመቻቹ ይህን ግዙፍ ደሴት አሁን በሚባለው በሦስት እጥፍ ለማስፋት ሐሳብ አለ።
ደሴቱ ከየብስ ርቀው ለሚተከሉ 200 ግዙፍ የንፋስ ተርባይኖች ማረፍያ ይሆናል ተብሏል።
በብልጽጓ ዴንማርክ ታሪክ እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክት ሲታለም የመጀመርያ ነው። ሰው ሠራሽ የኃይል ደሴቱ ዴንማርክን 210 ቢሊዮን ክሮነር ወይም 34 ቢሊዯን ዶላር ያስወጣታል ተብሎ ተገምቷል።
ከየብስ 80 ኪሎ ሜትር ርቆ ባሕር ላይ የሚገነባው የኃይል ደሴት ከፊሉ በመንግሥት እጅ ሲሆን የተቀረው ደግሞ ወደ የግል ዘርፍ ባለሀብቶች ይተላለፋል ተብሏል።
ይህ የኃይል ደሴት ለዴንማርካዊያን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገሮችም ጭምር ኃይል አቅርቦት ይሰጣል ተብሏል። ከዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ኃይል ያገኛሉ ከሚባሉት አገራት መሀል ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ታላቋ ብሪታኒያ ተጠቅሰዋል።
ግሪን ኃይድሮጂን ለባሕር ትራንስፖርት፥ ለአየር ትራንሰፖርትና ለከባድ ኢንዱስትሪዎችም የሚውል ይሆናል።
ዴንማርክ በታዳሽ ኃይል እጅግ ስኬታማ ከሚባሉ አገራት አንዷ ስትሆን በ2030 የግሪንሀውስ ልቀትን በ70 ከመቶ ለመቀነስ እየሰራች ነው።
ባለፈው ዓመት ዴንማርክ በሰሜን ባሕር ላይ ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት የነዳጅና የጋዝ ፍለጋ እንደማታደርግ ይፋ ማድረጓ አስደናቂ ዜና ሆኖ ነበር።
ፕሮፌሰር ኦስተርጋርድ በዚህ ጉዳይ ለቢቢሲ አስተያየት ሲሰጡ 'ዴንማርክ አስደናቂ ተግባር እየፈጸመች ነው። በንፋስ ኃይል በየብስ ላይ ከዓለም አንደኛ ነበረች፤ አሁን ደግሞ ወደ ባሕር ገብታለች፤ አሁን የኃይል ደሴት የሚባል ሐሳብ ለዓለም እያስተዋወቀች ነው፤ ይህም የዴንማርክ ኢንዱስትሪዎች ለዓለም ፈር ቀዳጅ ሆነው ይዘልቃሉ' ብለዋል
ባለፈው ኅዳር የአውሮጳ ኅብረት የባሕር ላይ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በ25 እጥፍ ለማሳደግ እቅዱን ይፋ አድርጎ ነበር። የአውሮጳ ኅብረት አባል አገራት አንድ ሦስተኛ የታዳሽ ኃይላቸውን የሚያገኙት ከንፋስ ነው።
ከኅብረት አገራቱ ውስጥ ዴንማርክ 1.7 ጌጋ ዋት ኃይል ከንፋስ በማቅረብ ቀዳሚዋ ናት














