በዓለም ግዙፉ የፀሐይ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ሊገነባ ነው

የፎቶው ባለመብት, HIVE ENERGY
በዓለም ከፀሐይ ብርሃን ከሚመነጩ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች አንዱ ይሆናል የተባለለትን ፕሮጀክት ዩናይትድ ኪንግደም ልትገነባ ነው።
880 ሺህ ፓናል የፀሐይ ብርሃን ተቀባይ ሰሌዳዎች የሚዘረጉበት ሜዳ የተዘጋጀ ሲሆን ይህም 890 ሄክታር ስፋት ይኖረዋል።
የፀሐይ ብርሃን ሰሌዳዎች ይዘረጉበታል የተባለው ቦታ በሰሜን ኬንት ጠረፍ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የገጠሩን ውበት ያጠፋል በሚል ፕሮጀክቱን ክፉኛ ተቃውመውታል። ፕሮጀክቱ ከ2017 ጀምሮ ሲያጨቃጭቅ ቆይቶ ከሦስት ዓመታት ክርክርና ንትርክ በኋላ መጽደቁ ተዘግቧል።
ይህ የፀሐይ ብርሃን ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለ91 ሺህ መኖርያ ቤቶች ኤሌክትሪክ ማቅረብ ይችላል። ከ350 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ያመነጫል። የፕሮጀክቱ ወጪ 450 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን እንደ ፈረንጆቹ በ2022 ሥራ ይጀምራል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ በዓለም ካሉ ግዙፍ የኃይል ማጠራቀሚያ ቋቶች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል። የኃይል ማጠራቀሚያ ቋቱ 20 የእግር ኳስ ሜዳዎች ቢዘረጉ የሚኖራቸው ስፋት ይኖረዋል።
ግንባታውን በጥምረት የሚያካሄዱት ሃይቭ ኢነርጂና ዊርሶል ኢንርጂ የተባሉ የሶላር ኃይል ተቋራጭ ኩባንያዎች ናቸው።
የአረንጓዴ መብት ተቆርቋሪዎች በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተለያየ አቋም የወሰዱ ሲሆን የዱር አራዊቶችን ሕይወትና ብዝሃነት ያዛባል የሚሉ አልጠፉም። ውብ የገጠር ሕይወትን ወደ ተራ ኢንዱስትሪ አውራጃ ገጽታ ይቀይረዋል ብለው የተቃወሙትም በርካታ ናቸው።
ፍሬንድስ ኦፍ ኧርዝ የተባለ የአረንጓዴና ልምላሜ ተቆርቋሪ ድርጅት ግን ፕሮጀክቱን ደግፎታል። ምክንያቱ ደግሞ የፀሐይ ብርሃን ተቀባይ ሰሌዳዎች የሚዘረጉበት ቦታ ለዘመናት የታረሰና በአረንጓዴ ቢሸፈንም ለሰደድ እሳት የሚጋለጥ በመሆኑ ነው።
"ይህን ለዘመናት የታረሰ መሬት ለምርት ለማብቃት በርካታ ማዳበሪያ ያስፈልጋል፤ ይህ ራሱን የቻለ ጉዳት ነው። ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መጠቀም ብልህነት ነው" ብሏል ድርጅቱ።
ፕሮጀክቱ ዩናይትድ ኪንግደም ታዳሽ ኃይልን ለመገንባትና ከበካይ የኃይል አቅርቦት ለመታቀብ የገባችው ቃል አንድ አካል ነው።












