አረንጓዴ የኃይል አማራጭ ነዳጅ አምራች አገራትን እስከ 13 ትሪሊየን ዶላር ሊያሳጣቸው ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ የወጣ አንድ አዲስ ሪፖርት ዓለም ወደ አረንጓዴ ኃይል ፊቷን ካዞረች ነዳጅ አምራች አገራት ከመንግሥታዊ ትርፋቸው ላይ በበርካታ ትሪሊዮን ዶላር ቅናሽ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ጠቁሟል።
በሪፖርቱ መሰረት በከፍተኛ ደረጃ ነዳጅ የሚያመርቱ አገራት ከአጠቃላይ መንግስታዊ ገቢያቸው ላይ ቢያንስ 40 በመቶ የሚሆነውን ሊያጡ ይችላሉ።
ሪፖርቱ አክሎም ዓለም ታዳሽ ኃይሎችን መጠቀም ከጀመረች በአውሮፓውያኑ 2040 ነዳጅ አምራች አገራት እስከ 13 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ሊያጋጥማቸው ይችላል።
መንግሥታት የዓለም የሙቀት መጠንን ለመቀነስ ከፍተኛ እንቅቃሴ በሚያደርጉበትና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በሚጥሩበት ወቅት ሪፖርቱ መውጣቱ አገራትን እንዳያስደነግጣቸው ተሰግቷል።
ጥናቱን የሰራው 'ካርበን ትራከር' የተባለው ተቋም ይህ መረጃ ለነዳጅ አምራች አገራትና ፖሊሲ አርቃቂዎች የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል ብሏል።
አገራቱ ገና ከአሁኑ ኢኮኖሚያቸውን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዲያከናውኑ እድል የሚፈጥር ነው ብሏል።
በ2040 ምናልባት የነዳጅ ፍላጎት አሁን ካለበት በእጅጉ ሊጨምር ይችላል ያለው ተቋሙ ነገር ግን ዓለም ፊቷን ወደ አረንጓዴ ኃይል ማዞሯ ስለማይቀር መልሶ ፍላጎቱ መቀነሱ አይቀርም ሲል ተንብይዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመጪዎቹ ዓመታት የአየር ጸባይ ለውጥን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ አምራች አገራትና የዘርፉ ባለሙያዎች ከሚፈልጉትና ከሚተነብዩት በታች ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ሪፖርቱ በመነሻነት የተጠቀመው መረጃ ዓለም መንግስታት የምድራችን የሙቀት መጠን ጭማሪ ከ1.65 ሴንቲግሬድ እንዳይበልጥ የሚስማሙ ከሆነ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ከምግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
13 ትሪሊየን ዶላር ሊያጡ ይችላሉ የሚለው ቁጥርም ሊገኝ የቻለው የነዳጅ ዋጋ እና ሽያጭ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ካልተቀየረ የሚለውን መሰረት በማድረግ ሲሆን ኢኮኖሚያቸው በነዳጅ ላይ ያልተመሰረቱ አገራትንም ያካተተ ነው ተብሏል።
በዚሁ ሪፖርት ላይ ከተካተቱትና ኢኮኖሚያቸው በነዳጅ ላይ ካልተመሰረቱት አገራት መካከል አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሕንድ እና ቻይና ተጠቃሽ ናቸው።
ነገር ግን የሪፖርቱ ዋነኛ ትኩረት የሆኑት ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ የነዳጅ ምርት ላይ የተንጠለጠሉ 40 አገራት ናቸው።
ከነዚህ አገራት መካከል ሳዑዲ አረቢያ ዋነኛዋ ስትሆን ከአጠቃላይ ዓመታዊ ትርፏ ውስጥ ነዳጅ 60 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል።
ኢራቅ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ደግሞ 80 በመቶ የሚሆነው ኢኮኖሚያቸው በነዳጅ ምርት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አንዳንድ አገራት ከሌሎች በተለየ መልኩ ተጎጂዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
አንጎላ እና አዘርባጃንን ጨምሮ ሰባት የሚሆኑ አገራት ቢያንስ እስከ 40 በመቶ የሚሆን ኪሳራ ያጋጥማቸዋል። ሳዑዲ አረቢያ፣ ናይጄሪያ እና አልጄሪያን ጨምሮ 12 የሚሆኑ አገራት ደግሞ ከ20 እስከ 40 በመቶ የሚሆን ኪሳራ ያጋጥማቸዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ አገራት ደግሞ የነዳጅ ምርታቸው ከሌሎቹ አገራት ሲነጻጸር አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት የሚኖረው ጫና የቀነሰ ሊሆን እንደሚችል ሪፖርቱ ጠቁሟል።
እንደ ጋና፣ ዩጋንዳ እና ጉያና ያሉ አገራት ደግሞ በቅርቡ ያገኟቸውን የነዳጅ ክምችቶች ከግምት በማስገባት በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት እናገኘዋለን ብለው ያሰቡት ትርፍ ከእጅጉ ሊቀንስ እንደሚችል ይገመታል።
ሪፖርቱ በመጨረሻም ኢኮኖሚያቸው በነዳጅ ላይ የተመሰረተ አገራትና ወደፊት በነዳጅ ላይ ተስፋቸውን የጣሉ አገራት ከአሁኑ ሌሎች አማራጮችን ማሰብ መጀመር አለባቸው ሲል አሳስቧል።
እንደ አማራጭ ካቀረባቸው መካከል ደግሞ ትምሀርት ላይ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስ፣ ንግድና የምርት ዘርፉን ማሳደግ እንዲሁም አማራጭ የኃይል መንገዶችን መፈለግ የሚጠቀሱ ናቸው።












