የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ የጠፋ ውሻውን ላገኘለት ራፐር 30 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተፈረደበት

ታትሟል

የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች ዳንኤል ሰተሬጅ ከሁለት ዓመታት በፊት ጠፍታ የነበረቸውን ሉሲ የተሰኘች ውሻውን ላገኘለት ግለሰብ 30 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ፍርድ ቤት ወሰነበት።

አሁን በአውስትራሊያ ላለ ክለብ የሚጫወተው ዳንኤል፤ ሉሲ የተሰኘች ውሻው በሎስ አንጀለስ ከሚገኘው ቤቱ መሰረቋን ተከትሎ ነበር ላገኛት ሰው ወረታውን ለመክፈል ቃል የገባው።

ኪላ ፌም በሚለው የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ፎስተር ዋሽንግተን የተሰኘው ራፐር ውሻውን አግኝቶ ለዳንኤል ቢሰጠውም ቃል የተገባው ክፍያ ግን እንዳልተፈጸመለት ተናግሯል። ይህንን ማመልከቻ ተከትሎም ችሎቱ ለዋሽንግተን ፈርዶለታል።

ፒኤ በተሰኘው የዜና ወኪል እጅ የገቡት የችሎቱ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ፍርዱ ዳንኤል ወደ ችሎት ቀርቦ ምላሽ ሳይሰጥበት በፊት ነው የተሰጠው።

ዳኛው እግር ኳስ ተጫዋቹ ለራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ከ30 ሺህ ዶላሩ ክፍያ በተጨማሪ ደረሰብኝ ያለው የመገፋት ስሜት ላደረሰበት ጉዳት የ85 ዶላር ካሳ እንዲከፍለውም አዟል።

"ገንዘቡን እንደሚከፍል እና ወደ ይግባኝ እንደማይሄድ ተስፋ አደርጋለሁ። በጣም ደስ ብሎኛል። ለዚህ የፍርድ ቤት ጉዳይ ከአንድ ዓመት በላይ ስከራከር ቆይቻለሁ። ውሻውን ሳገኝ ሕይወቴ የተወሰነ ይሻሻላል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር" ሲልም ዋሽንግተን ተናግሯል።

በእግር ኳስ ተጫዋቹ የሆሊዉድ ቤት ውስጥ ተገጥመው በነበሩ የደኅንነት ካሜራ ቪዲዮዎች ኮፍያ ያለው ሹራብ ያደረጉ ሦስት ሰዎች ውሻዋ በጠፋችበት ጊዜ ላይ ታይተው ነበር።

"ለውሻዋ ማንኛውንም ነገር እንከፍላለን" ሲል ዳንኤል ስተርጅ ተናግሮ ነበር።

"ማንም ይሁን ማን ውሻዬን ካመጣልኝ ከ20 እስከ 30 ሺህ ዶላር እከፍላለሁ" ሲልም ገልጾ ነበር። ይህንን ካለ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር ውሻውን ያገኘው።

የቀድሞው የሊቨርፑል ቡድን ተጫዋቹ ወኪሎች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።