በኡጋንዳ የሽብር ጥቃት ከተከሰሱ 15 ግለሰቦች መካከል ነፍሰጡር እንደምትገኝበት ተገለጸ

በህዳር ወር የደረሰው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በኡጋንዳ በተፈጸሙ በርካታ ጥቃቶች እጃቸው አለበት የተባሉ ነፍሰጡርን ጨምሮ 15 ሰዎች በሽብርተኝነት ተከሰሱ።

አብዛኛዎቹ ተከሳሾች የእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይ ኤስ) አካል የሆነው 'አላይድ ዲሞክራቲክ ፎርስ' (ኤዲኤፍ) የተሰኘው ታጣቂ ቡድን አባላት ናቸውም ተብሏል።

ባለስልጣናቱ እንዳሉት ቡድኑ በቅርብ ጊዜ በኡጋንዳ ከተከሰቱት አራት የቦምብ ጥቃቶች እጁ አለበት።

ኡጋንዳ በአጎራባቿ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባሉ በኤዲኤፍ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምራለች።

ታጣቂው ቡድን የተቋቋመው መንግሥት በሙስሊሙ ላይ በሚወስደው እርምጃ ቅር በተሰኙ ኡጋንዳውያን በአሮፓውያኑ 1990ዎቹ ነው።

ቡድኑ በደረሰበት ወታደራዊ ጥቃት መቀመጫው ከሆነው ከአገሪቷ ምዕራብ ተራራማ ርዌንዞሪ ግዛት ተጠራርጎ የወጣውም በ2000ዎቹ ነበር።

ተዋጊዎቹ በአካባቢው የሚገኙ መንደሮችን አጥቅተዋል እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን አቃጥለዋል ተብለው ይወቀሳሉ።

በጥቅምት ወር የተፈጸሙ ጥቃቶች እንዲሁም በህዳር ወር በመዲናይቱ ካምፓላ ሶስት የአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ጥቃቶች ቡድኑ ዘዴውን ቀይሯል የሚል ስጋት በባለስልጣኖቹ ዘንድ እንዲፈጠር አድርጓል።

ፖሊስ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደገለጸው 15ቱ ተጠርጣሪዎች በሽብርተኝነት፣ ሽብርተኝነትን በመርዳት እንዲሁም የሽብር ቡድን አባል በመሆን ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ ቀነ ቀጠሮ ጥር መጀመሪያ ላይ የሰጠ ሲሆን እስከዚያው ድረስም በእስር እንደሚቆዩ ታውቋል።

ተከሳሾቹ እስካሁን ድረስ አቤቱታ አላቀረበም።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ኡጋንዳ በኤዲኤፍ ታጣቂዎች ላይ በምስራቃዊው ክልል የአየር ድብደባ እና የምድር ጦርን ያካተተ ጥቃት እንዲከፈት ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠይቃ የነበረ ሲሆን ኮንጎም ይህንን በእሺታ ተቀብላዋለች።