ምሳ ለመብላት ፈቃደኛ ባለመሆኗ የሦስት ዓመት ህፃን የገደለው ግለሰብ በእስር ተቀጣ

ፖል ማርሽ

የፎቶው ባለመብት, Kent Police

ታትሟል

የሴት ጓደኛውን የሦስት ዓመት ህፃን ልጅ ምሳ አልበላም በማለቷ የገደለው ግለሰብ በአስራ አንድ ዓመት እስር ተቀጣ። ህፃኗ የአካል ጉዳተኛ ነበረች።

በእንግሊዝ የኬንት ከተማ ነዋሪ የሆነው የ27 ዓመቱ ፖል ማርሽ ጄሲካ ዳልጌሊሽ የተባለችው ህፃን ምሳ አልበላም በማለቷ ተናዶ ክፉኛ እንደበደበባትም በፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ ያስረዳል።

ከዚያም ከደረጃ ላይ ወድቃ ነው በሚልም ጥቃቱን ለመሸፋፈን ሞክሮ ነበር።

ፖል ማርሽ ከዚህ ቀደም በሜይድስቶን ክራውን ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በልጆች ጭካኔ እና ግድያ ተከሷል።

ጄሲካ በአውሮፓውያኑ 2019 የገና ዋዜማ ላይ በሆስፒታል ውስጥ ነው ህይወቷ ያለፈው።

በክሱ መሰረት የእንክብካቤ ሠራተኛ የሆነው ፖል በከፍተኛ ጉልበት ህፃኗን ሲወረውራት ጭንቅላቷ ጠንካራ ከሆነ የአልጋ ጣውላ፣ ወለል ወይም ግድግዳ ጋር እንደተጋጨች የተደረገላት ምርምራ ያሳያል።

"ህመም እና ስቃይ"

የጄሲካ እናት ለፍርድ ቤቱ በሰጠችው ቃል ልጇን የነጠቃትን ግለሰብ "እንስሳ" እና "ጭራቅ" ብላ ጠርታዋለች።

"እሷን የነጠቀኝን ጭራቅ በቀሪው አስከፊ ህይወቱ በየቀኑ እንዲሰቃይ እማጸናለሁ" ብላለች።

"ልጄን ከማጣቴ ህመም ፈጽሞ አላገግምም። ጄሲካ በዓለም ላይ ያለች ብርሃኔ ነበረች" ብላለች

"መላው ቤተሰብ ጄሲካ ገና በለጋነቷ በመቀጠፏ ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቶታል። የሞቷ ምክንያት ደግሞ ሐዘናቸውን የበለጠ ድርብርብ ያደርገዋል። ስቃያቸው ጥልቅ ነው" በማለት ብያኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ካቫናግ ተናግረዋል።

"የዚህች ተወዳጅ ትንሽ ልጅ ሞት ለብዙ ሰዎች ከፍተኛ ስቃይ እንደፈጠረ ግልጽ ነው" በማለትም አክለዋል።

ግለሰቡ ህይወት በማጥፋት የዘጠኝ ዓመት እስራት እና ተጨማሪ ሁለት ዓመት በህፃኗ ላይ በፈጸመው የጭካኔ ድርጊት ተፈርዶበታል።