ዴንማርክ በዓመት 15 ሚሊዮን ዩሮ በመክፈል ከኮሶቮ እስር ቤት ተከራየች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ዴንማርክ የገጠማትን የእስር ቤቶች መጨናነቅ ችግር ለማቅለል 300 የእስር ክፍሎችን ከኮሶቮ ለመከራየት ከስምምነት ላይ ደረሰች።
ሁለቱ አገራት በደረሱት ስምምነት መሠረት ዴንማርክ ለምትከራያቸው የእስረኞች ክፍሎች ለመጀመሪያ አምስት ዓመታት በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ዩሮ የምትከፍል ሲሆን፣ በተጨማሪም አገሪቱ በካይ ጭስ የሌለው የኃይል አቅርቦት እንዲኖራት ታግዛለች።
ዴንማርክ የምትከራያቸውን እነዚህን የእስር ክፍሎች ከአውሮፓ አገራት ውጪ መጥተው በአገሯ ውስጥ ወንጀል የፈጸሙና ፍርዳቸውን ሲጨርሱ ከዴንማርክ የሚባረሩ እስረኞችን ለማቆየት ትጠቀምባቸዋለች።
በግዛቷ ውስጥ ጥቅም ላይ የማይውሉ እስከ 800 የሚደርሱ የእስረኛ ክፍሎች ያሏት ኮሶቮ፣ ለኪራይ ባቀረበቻቸው እስር ቤቶች ውስጥ የዴንማርክ ሕጎች ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሏል።
ሁለቱ አገራት ለአምስት ዓመታት የሚቆየውን የእስር ቤት ኪራይ ስምምነት ሰኞ ዕለት መፈራረማቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው ያስታወቁት።
ኮሶቮ ለዴንማርክ ለምታከራያቸው የእስረኞች ክፍሎች በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ በአጠቃላዩ 210 ሚሊዮን ዩሮ ይከፈላታል።
"ይህ ስምምነት በእስር ቤት ጠባቂዎቻችን ላይ ያለውን ጫና ከማቅለሉ ባሻገር ከሦስተኛ አገር መጥተው ከዴንማርክ እንዲወጡ የተወሰነባቸው ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ ቦታ እንደማይኖራቸው ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል" ብለዋል የዴንማርክ የፍትሕ ሚኒስትር ኒክ ሔከራፕ በሰጡት መግለጫ።
ውሳኔውን በተመለከተ በሁለቱም አገራት ያሉ አክቲቪስቶች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ዴንማርክ የማትፈልጋቸውን የውጭ አገር እስረኞችን ወደ ሌላ አገር መላክ የለባትም የሚሉና ሌሎች ደግሞ ግለሰቦቹን ከቤተሰባቸው አርቆ ማሰር ተገቢ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።
የኮሶቮ ፍትሕ ሚኒስትር እንደተናገሩት የተፈደባቸው አደገኛ ወንጀለኞችና የሽብር ወንጀል ተጠያቂዎች እንዲሁም በማይድን በሽታ የሚሰቃዩ እስረኞች ከዴንማርክ ወደ አገራቸው እንደማይላኩ ገልጸዋል።
ኮሶቮ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አካል ከነበረችው ሰርቢያ በተናጠል ነጻነቷን ያወጀችው በአውሮፓውያኑ 2008 ነበር።
እስረኞችን በሌላ አገር በሚገኝ የኪራይ እስር ቤት ማቆየት አውሮፓ ውስጥ እምብዛም አዲስ ነገር አይደለም። ከዚህ በፊት ኖርዌይና ቤልጂየም ኔዘርላንድስ ውስጥ የእስረኛ ከፍሎችን ተከራይተዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዴንማርክ ውስጥ ያለው የእስረኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን እስር ቤቶችን የሚጠብቁ መኮንኖች ቁጥር ደግሞ እየቀነሰ ነው።
ከአምስት ዓመት ወዲህ በዴንማርክ ውስጥ ያሉት የእስረኞች ቁጥር ከ3,400 ወደ 4,200 ያደገ ሲሆን የእስር ቤት ጠባቂዎች አሀዝ ደግሞ ከ2,500 ወደ 2,000 ቀንሷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዴንማርክ ከስደተኞች አንጻር ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን እየወሰደች ሲሆን በርካታ ክልከላዎችንም ተግባራዊ አድርጋለች።












