ለአፍሪካውያን ቤተሰቦች ከፍተኛ ወጪያቸው የትምህርት ቤት ክፍያ ነው-ተመድ

ታትሟል

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት የሚኖሩ ቤተሰቦች ከወጪያቸው ከፍተኛውን የሚይዘው የትምህርት ቤት ክፍያ እንደሆነ ዩኔስኮ አዲስ ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በርካቶች ለትምህርት ጥራት በሚል ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፍሉም ሪፖርቱ ያትታል።

ለምሳሌ በጋና የአንድ ቤተሰብ በአማካይ 13 በመቶ የሚሆነው ወጪ የሚውለው ለትምህርት ነው።

በአጠቃላይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ለትምህርት ከሚወጣው ገንዘብ 40 በመቶውን የሚጠጋው የሚሸፍኑት ቤተሰቦች ናቸው።

እንደ መንግሥት ካሉ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በበለጠ የቤተሰብ ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብሏል ሪፖርቱ።

ባለፈው አርብ ይፋ በተደረገው የግሎባል ኤዱኬሽን ሞኒተሪንግ (ጂኢኤም) ሪፖርት መሰረት ዩኔስኮ ትምህርትን በመስጠት ረገድ አለመመጣጠን እና የመገለል ስጋት እየጨመረ መሆኑን አሳውቋል።

የሪፖርቱ ዳይሬክተር የሆኑት ማኖስ አንቶኒኒስ የኮቪድ-19 ተፅእኖ የቤተሰብ ገቢ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ሲሆን ከዚህም ጋር በተያያዘ የትምህርት ቤት ክፍያዎችን እና ሌሎች ወጪዎች ለመሸፈን ለብዙዎች አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።

ሪፖርቱ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ 8 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ ገንዘብ እንደሚበደሩም አስፍሯል።

እንደ ዩጋንዳ እና ኬንያ ባሉ አገራት የከፋ መሆኑንን የጠቆመው ሪፖርቱ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ቤተሰቦች የትምህርት ቤት ክፍያን ወጪ ለመሸፈን ብድር እንደሚወስዱ ነው።

በነዚህ አገራት የትምህርት ቤት ክፍያ በጣም ከፍተኛ መሆኑንም አስቀምጧል።

ዩኔስኮ ለ12 ዓመታት ያህል ነፃና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ለማዳረስ መንግስታት የበለጠ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው ጠይቋል።

በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች ከፍለው ማስተማር ለማይችሉት እንዲያስቡም ጠይቋል።