በሱዳን ዳርፉር ግዛት በተነሳ ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች ተገደሉ

በምዕራብ ሱዳን ዳርፉር ግዛት ለቀናት በዘለቀ የብሄር ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች ተገደሉ።
በአረብ ጎሳዎች እና በቀድሞ አማፂያን የሚደገፉት የአፍሪካ ማሳሊት ማህበረሰብ ተዋጊዎች መካከል ውጊያ ለቀናት ሲደረግ ቆይቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው በክሪኒክ ግዛት አካባቢ ባለው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የተወሰኑትም ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት አገር ቻድ መግባታቸው ተገልጿል።
ከግጭቱ የተረፉ ግለሰቦች እንደተናገሩት ታጣቂዎች ከክሬኒክ በስተምዕራብ በሚገኝ መንደር ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል፤ እንዲሁም ቤቶችን ከማቃጠላቸው በፊት ተኩስ ከፍተዋል።
በዋናው መንገድ ላይም አድፍጠው ህዝቡ ወደሌሎች ቦታዎች እንዳይሻገር ዘግተው ነበር ተብሏል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ማግኘት አልቻሉም።
በባለፈው ሳምንት መጨረሻ እሁድ እለት በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል በተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት በትንሹ 55 ሰዎች ተገድለዋል።
ማክሰኞ እለት በአካባቢው በሚገኝ ቁጥቋጦ ውስጥ ተጨማሪ አስከሬኖች የተገኙ ሲሆን የሟቾችንም ቁጥር ከ100 በላይ አድርሶታል። ከዚህም በተጨማሪ በደርዘን የሚቆጠሩ ደብዛቸው የደረሰበት አልታወቀም።
ባለፈው ወር በምእራብ ዳርፉር በተለያዩ አካባቢዎች 43 ሰዎች ተገድለዋል።
በግጭት በምትናጠው ዳርፉር ደቡባዊ ግዛትም ብሄር ተኮር ግጭቶች መከሰታቸውም ታውቋል።
መንግስት ብጥብጡን ለመቆጣጠር የመከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይልና፣ የፖሊስ ጥምር ሃይል ወደ ምዕራብ እና ደቡብ ዳርፉር አሰማርቷል።












