ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ 6 አገራት በኢትዮጵያ ማንነትን መሠረት ያደረገ እስር እንዳሳሰባቸው ገለጹ
አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ ስድስት አገራት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርን መሠረት ያደረገ እስር መበራከቱ "በእጅጉ አሳስቦናል" ሲሉ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን "ብሔራቸውን መሠረት በማድረግ ያለ ክስ እያሰረ ነው" ያሉት አገራት አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ድረ ገጽ ላይ የወጣው የስድስቱ አገራት መግለጫ እንደሚለው፤ እነዚህ አገራት በኢትዮጵያ ያለው የትግራይ ተወላጆች እስር እጅጉን አሳስቧቸዋል።
"የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአንድ ብሔር ተወላጆችን ለይቶ ለማሰር እንደ ምክንያት ሊውል አይችልም" ሲሉ አገራቱ ስጋታቸውን አስረግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን ሪፖርትን እንደ ማስረጃ ያጣቀሱት አገራቱ፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀሳውስት፣ አረጋውያን፣ እናቶች ከነልጆቻቸው እንዲሁም ሌሎችም የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
"ሰዎች ሳይከሰሱ እየታሰሩ ነው። ፍርድ ቤትም አይቀርቡም። ታስረው የሚገኙት በኢ-ሰብአዊ ሁኔታ ውስጥ ነው" ይላል መግለጫው።
አንድ ዓመት ያለፈው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ እስር እተካሄደ መሆኑን በመግለጽ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ሪፖርት ሲያወጡ ነበር።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና ፖሊስ በሰጡት ምላሽ፤ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ማንነትን መሠረት ያደረገ ሳይሆን ከሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት ባላቸውና ማስረጃ በተገኘባቸው ላይ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የትግራይ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም መያዛቸውን ገልጸዋል።
ስድስቱ አገራት በጋራ ያወጡት መግለጫ፤ የዜጎች እስር ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጻረር ጠቁሞ በአፋጣኝ እንዲቆም አሳስቧል።
አያይዘውም "ዓለም አቀፍ አካላት በአፋጣኝ ያልተገደበ ጉብኝት እንዲያደርጉ መፈቀድ አለበት" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ እየደረሱ ያሉ ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚያወግዙ አገራቱ አስታውቀዋል
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሸን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) ጋር በጋራ ያደረጉትን ምርመራ ተከትሎ የወጣው ሪፖርት በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ወሲባዊ ጥቃት መፈጸማቸውን አረጋግጧል።
"አሁንም የግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም አካላት የሚፈጸሙ ጥሰቶች ሪፖርት እየተደረጉ ነው" ይላል መግለጫው።
ሁሉም ወገኖች ንጹሀን ዜጎችን፣ የሰብአዊ መብት ሠራተኞችን እና ሐኪሞችን በመጠበቅ ረገድ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እንዲያከብሩም ጠይቀዋል።
ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለ ግልጽ ነው ያሉት ስድስቱ አገራት፤ "ከዚህ ቀደም የደረሱ፣ አሁን እየደረሱ ያሉ እና ለወደፊትም የሚደርሱ የንጹሀን ጥቃቶችን እናወግዛለን" ሲሉ አክለዋል።
ሁሉም ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ወደ ድርድር እንዲመጡ ከመምከራቸው ባሻገር፤ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ እንዲወጣም አሳስበዋል።
"ኢትዮጵያውያን ሁሉን አካታች የፖለቲካ ውይይት እና ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ይገባቸዋል። የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙም ተጠያቂ መደረግ አለባቸው" ይላል መግለጫው።
በጦርነቱ ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በግልጽ ባይታወቅም በበርካታ ሺዎች እንደሚቆጠሩ ይገመታል።
የመሠረተ ልማት አቅርቦት ላይ ከደረሰው ውድመት ባሻገር፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።