ፓራግ አግራዋል፡ ህንድ ለአዲሱ የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙገሳ እየቸረች ነው

የፎቶው ባለመብት, TWITTER
ህንድ የተወለደው ፓራግ አግራዋል የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተብሎ በመሾሙ በተወለደበት አገር ብዙዎች ሙገሳ ሲቸሩት ርዕሰ ዜናም ሆኗል።
የ37 ዓመቱ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ሰኞ ዕለት ሥራውን መልቀቁን ያስታወቀውን የትዊተር መስራች የነበረውን ጃክ ዶርሲን ተክቷል።
አግራዋል ትዊተርን የተቀላቀለው እአአ በ2011 ሲሆን በተለየዓዩ የሥራ እርከኖች በማለፍ እስከ ዋና የቴክኖሎጂ ኃላፊነት ሠርቷል።
አስተማማኝ ተብሎ የተገለጸ ሲሆን ከፊት ትልቅ ሥራ ይጠብቀዋል ተብሏል።
የሹመቱ ዜና ከ30 ሚሊዮን በላይ የትዊተር ተጠቃሚዎች ባሉባት ህንድ ብዙ ደስታን ፈጥሯል ።
ብዙዎች በትዊተር ገጻቸው ስለሹመቱን ደስታቸውን ገልጸው የS&P 500 ኩባንያ ትንሹ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሆኑን ጠቁመዋል። አንዳንዶቹም ህንዳዊያን ከሆኑና በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከሚሠሩት ዝርዝር ውስጥ ጨምረውታል።
ዶርሲ ሰኞ ዕለት በትዊተር ገጹ በሰጡት መግለጫ "ፓራግ ይህንን ኩባንያ ለመቀየር ከረዱት ሁሉም ወሳኝ ውሳኔዎች በስተጀርባ ነበር። እሱ የማወቅ ጉጉት ያለው፣ ጠያቂ፣ ምክንያታዊ፣ ፈጣሪ፣ ራሱን የሚያውቅ እና ትሁት ነው። እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በእሱ ላይ ያለኝ እምነት ጥልቅ ነው" ብሏል።
አግራዋል በበኩሉ "ስለወደፊቱ በጣም ደስ ብሎኛል" በማለት በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
"አመሰግናለሁ ጃክ። ክብር ይሰማኛል። አብሮኝ ለዘለቀው ምክርህ እና ጓደኝነትህ ምስጋናዬ ይድረስህ። ከ10 አመት በፊት ከ1,000 ያነሱ ሠራተኞች በነበሩበት ወቅት ነበር ኩባንያውን የተቀላቀልኩት። አስር ዓመት ቢሆንም ለእኔ እንደ ትናንት እንደሆነ ይሰማኛል" ሲል ጽፏል።
ከታዋቂው የህንድ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (አይኤይቲ) የተመረቀው አግራዋል ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በኮምፒውተር ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪውን አግኝቷል።
ትዊተርን ከመቀላቀሉ በፊት በማይክሮሶፍት፣ ያሁ እና ኤቲ ኤንድ ቲ በተለያዩ የምርምር ዘርፎች ላይ ሠርቷል።
ቀደም ሲል የሠራቸው ሥራዎች በሙሉ ከዓይኖች የራቁ ቢሆኑም አዲሱ ሹመቱ አግራዋልን በአንድ ጀምበር ወደ ታዋቂነት አሸጋግረውታል። በመሆኑም አሁን የሚያደርገው እያንዳንዱ እርምጃ በጥንቃቄ የሚከታተሉት ይበዛሉ።
ከወዲሁም እአአ በ2010 ከዴይሊ ሾው ወስዶ ያሰፈረው የትዊተር መልእክት በአንዳንዶች ግራ ዘመም ስለመሆኑ እንደማስረጃ እየተጠቀሙበት ሲሆን ብዙዎችም ዘረኛ ብለው ገልጸውታል። አግራዋል በጉዳዩ ላይ ምንም የሰጠው ይፋዊ መግለጫ የለም።
ሹመቱ የተሰማው ትዊተር እና የህንድ መንግሥት በማህበራዊ ሚዲያው የመናገር ነጻነት እና የሃሰተኛ ዜናዎች ዙሪያ ውዝግብ ውስጥ በገቡበት ሰዓት ነው።












