ኮቪድ፡ የሆላንድ ፖሊስ ከለይቶ ማቆያ ሆቴል ያመለጡ ጥንዶችን በቁጥጥር ሥር አዋለ

ታትሟል

የሆላንድ ፖሊስ ከኮቪድ ለይቶ ማቆያ ሆቴል ያመለጡ ጥንዶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

ፖሊስ ጥንዶቹን በቁጥጥር ሥር ያዋለው እሁድ ዕለት ከአምስተርዳም ስኪፖል አየር ማረፊያ ወደ ስፔን ሊበር ከነበረ አውሮፕላን ውስጥ ነው።

ስፔናዊው እና ፖርቹጋላዊቷ ግለሰቦች በፖሊስ ከተያዙ በኋላ ለአገሪቷ የጤና አገልግሎት ተላልፈው መሰጠታቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ይህ የሆነው ባለፈው ሳምንት በሁለት በረራ ከደቡብ አፍሪካ ተነስተው አምስተርዳም የገቡ 13 ሰዎች በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

አስራ ሦስቱ ግለሰቦች ኮቪድ-19 ከተገኘባቸው 61 ግለሰቦች መካከል ናቸው።

ይሁን እንጂ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጥንዶች ከእነዚህ መንገደኞች መካከል ይሁኑ አይሁኑ ታወቀ ነገር የለም።

የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ግን ጥንዶቹ አሁን ላይ ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ መንገደኞች ራሳቸውን ለይተው ከሚያቆዩበትና በሰሜን ምዕራብ ኬኔመርላንድ ግዛት ውስጥ ከሚገኝ ለይቶ ማቆያ ማምለጣቸውን ዘግበዋል።

ጥንዶቹ የሆላንድን የለይቶ ማቆያ ሕግ በመጣስ ሊከሰሱ እንደሚችሉም 'ዲ ቴሌግራፍ' የተባለው ጋዜጣ አስነብቧል።

በሆላንድ በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩና በአዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ስጋት ምክንያት የተጣለው ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ እሁድ ጠዋት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

የመጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እና ሱቆች የሥራ ሰዓት ለበርካታ ሳምንታት የተገደበ ሲሆን ቀድሞ ከነበራቸው የሥራ ሰዓት ቀድመው መዝጋት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቤት ውስጥ የሚያስተናግዱት የእንግዳ ብዛትም ተወስኗል።

ሰዎች በሚቻለው መጠን ከቤት ሆነው እንዲሰሩም እየተበረታታ ሲሆን የሕጻናት ማቆያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ግን ክፍት ናቸው።.

በአገሪቷ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ የተደረገውን ውሳኔ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በኔዘርላንድስ ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ይሁን እንጂ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከአንድ ሚሊየን ሕዝብ መካከል በአገሪቱ የተመዘገበው ሞት 1ሺህ 124 ሲሆን ከምዕራብ አውሮፓ ዝቅተኛ የሞት ቁጥር ከተመዘገበባቸው አገራት አንዷ ናት።

ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ መገኘቱን ደቡብ አፍሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ያሳወቀችው ረቡዕ ዕለት ነበር።

እስካሁን የወጡ መረጃዎችም ቫይረሱ ድጋሚ የመያዝ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ያመለከቱ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅትም ቫይረሱን "አሳሳቢ" ብሎታል።