እስራኤል የፍልስጥኤም የሲቪል ማህበራትን በሽብርተኝነት መፈረጇ ቁጣን ቀስቅሷል

ፍልስጥኤማውያን ተቃውሞ በማድረግ ላይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ከ100 የሚበልጡ ታዋቂ ሙዚቀኞች እና ጸሃፊዎች እስራኤል ስድስት የፍልስጥኤም የሲቪል ማህበራትን አሸባሪ ስትል መፈረጇን ተከትሎ ቁጣቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

«በፍልስጥኤማዊያን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የተከፈተ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተግባር» ሲሉ ነው በመግለጫው ላይ ያስታወቁት።

እስራኤል በበኩሏ እነዚህ የሲቪል ማህበራት በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኘው እና አደገኛ ጥቃቶችን የሚሰነዝረው የፒ.ኤፍ.ኤል.ፒ አካል ናቸው ስትል ወንጅላቸዋለች።

ተቋማቱ ከእስራኤል መንግሥት የቀረበባቸውን ክስ አጥብቀው ተቃውመዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ላይ የተወሰደው ይህ ፍረጃ ጽህፈት ቤቶታቸውን ሊያዘጋ እንዲሁም ሰራተኞቻቸውን ለእስር ሊዳርግ የሚችል መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ትችትን እያስተናገደ ይገኛል።

እስራኤል አሸባሪ ስትል የጠራቻቸው አል-ሃቅ፣ አዳሜር፣ አለማቀፍ የህጻናት መከላከያ፣ ቢሳን ሴንተር ፎር ርሰርች ኤንድ ዴቨሎፕመንት፣ የግብርና ስራዎች ኮሚቴ ማሕበር እና የፍልስጤም ሴቶች ኮሚቴ ማሕበር የተሰኙትን ነው።

«ይህ ፍረጃ የሲቪል ማሕበራቱን ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ የፍልስጥኤም የሲቪል ማሕበራትን እንዲሁም የሚያገለግሏቸውን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማዊያንን ጭምር አደጋ ላይ የሚጥል ነው» ሲሉ የሲቪል ማህበራቱ ተናግረዋል።

በዩኬ የእስራኤል አምባሳደር « በሌላ ተግባራት ላይ የተሰማራ የሽብር ቡድን አሁንም ቢሆን የሸብር ቡድን ነው» ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

«በእነዚህ ተቋማት ላይ የተወሰደው ውሳኔ በበቂ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ እንዲሁም ከህጉ ጋር በማይጣረስ መልኩ የተወሰደ ሲሆን በሕጉ መሰረት ተመልሶ ሊታይም ይችላል» ሲሉም አክለዋል።

«ሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ የእስራኤል ዴሞክራሲ ዋነኛ አካል ሲሆን እስራኤልም በሰብአዊ መብቶች ተቋማቶቿ አማካኝነት ያላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚታወቅ ነው» ብለዋል አምባሳደሩ።

ባሳለፍነው ሳምንት የእስራኤል መከላከያ እና የውጪ ሚኒስትሮች አንድ ስፔናዊት ሴት ለወታደራዊ ፍርድ ቤት በወንጀል ሃላፊነት ድርድር ወቅት የጤና ሰራተኞች ኪሚቴ ማህበር ለተሰኘ አንድ የሲቪል ማሕበር ገንዘብ ማሰባሰቧን ማመኗን እንደ ማስረጃ አድርገው አቅርበዋል።

እስራኤል ይህንንም ማሕበር ባለፈው አመት በተመሳሳይ እስራኤልን እንደ አገር ከማይቀበለው አክራሪው ፒ.ኤፍ.ኤል.ፒ ጋር አብሮ ሰርቷል በማለት በአሸባሪነት ፈርጃው ነበር።