ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አጥፍቶ ጠፊዎች በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ውስጥ የቦንብ ጥቃት ፈጸሙ
አጥፍቶ ጠፊዎች የኡጋንዳን ዋና ከተማ ካምፓላን ኢላማ አድርገው በፈጸሟቸው የቦምብ ጥቃቶች ቢያንስ ሦስት ሰዎችን ሲገድሉ ከ30 በላይ የሚሆኑትን ማቁሰላቸውን ፖሊስ ገለጸ።
ሦስት አጥፍቶ ጠፊዎች በሞተርሳይክሎች ላይ ሆነው በአገሪቱ ፓርላማ እና በከተማዋ ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ ባፈነዷቸው ቦምቦች ነው ጥቃቱን የፈጸሙት።
በፍንዳታው ሳቢያ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመኖራቸው የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ።
የኡጋንዳ ባለሥልጣናት ለተፈጸሙት የፍንዳታ ጥቃቶች መቀመጫውን ዴሞክራቲክ ኮንጎ ያደረገውን 'አላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስስ' ተብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ አድርገዋል።
ጥቃቶቹ የተፈጸሙስት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ሲሆን ተጨማሪ በርካታ ቦምቦች በካምፓላ ከተማ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ መገኘታቸውን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
"የቦምብ ፍንዳታ በተለይም የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ስጋቶች አሁንም አለ" ሲሉ የፖሊስ ቃል አቀባይ ፍሬድ ኢናንጋ ጠቅሰው "የዚህ የአገር ውስጥ ሽብርተኛ ቡድን በተለይም በአላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስስ የተቋቋመ የአጥፍቶ ጠፊ ቡድን በርካታ አባላት እንዳሉ እንምናለን" ብለዋል።
በዛሬው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ከሞቱት ሦስት ሰዎች በተጨማሪ አምስት በአስጊ ሁኔታ የቆሰሉትን ጨምሮ 33 ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ሊካሄዱ የነበሩ ስብሰባዎች የተሰረዙ ሲሆን የፓርላማው አባላትም ወደ ምክር ቤቱ ህንጻ እንዳይመጡ ተነግሯቸዋል።
በፍንዳታው ወቅት በፓርላማው አቅራቢያ ቆመው የነበሩ ተሽከርካሪዎች በእሳት የተያያዙ ሲሆን፣ በፖሊስ ጣቢያው አቅራቢያ ያሉ ህንጻዎች መስታወታቸው ተሰባብሯል።
ፖሊስ እንዳለው ጥቃቶቹ የተፈጸመው ከአላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስስ ጋር ግንኙነት ካለው "የአገር ውስጥ የሽበር ቡድን" ነው ብሏል።
ይህ ቡድን ኡጋንዳን ለረጅም ጊዜ እየመሩ ያሉትን ዩዌሪ ሙሴቪኒን በመቃወም በፈረንጆቹ 1990ዎቹ የተመሰረተ ነው።
አላይድ ዴሞክራቲክ ፎርስስ ባለፈው ጥቅምት ወር በአንድ ቡና ቤት ላይ ተፈጽሞ አንድ የ20 ዓመት አስተናጋጅን የገደለውን የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን አምኗል።
በጥቅምት ወር በአንድ አጥፍቶ ጠፊ በአውቶብስ ላይ ተጨማሪ የቦምብ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን በዚህም ጥቃት የፈጻሚው ህይወት አልፏል።