በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸው ሦስት የጽንፈኛ ቡድን አባላት ከኬንያ እስር ቤት አመለጡ

ከእስር ካመለጡት አንዱ የሆነው መሐመድ አሊ አቢካር የ41 ዓመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኝ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከእስር ካመለጡት አንዱ የሆነው መሐመድ አሊ አቢካር የ41 ዓመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኝ ነበር።
ታትሟል

በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸው ሦስት እስላማዊ ታጣቂዎች ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ማምለጣቸውን የኬንያ ፖሊስ አስታወቀ።

አደገኛ የተባሉት ሦስቱ እስረኞች ከመዲናዋ ናይሮቢ አቅራቢያ ከሚገኘው እና ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ማምለጣቸውን ተከትሎ ሰባት የእስር ቤቱ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ከእስር ካመለጡት መካከል አንዱ እአአ 2015 በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ በደረሰው የሽብር ጥቃት ተሳታፊ ነው ተብሎ የተፈረደበት ሞሐመድ አሊ አቢካር ይገኝበታል። በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥቃት ከ148 ሰዎች በላይ ተገድለዋል።

ባለሥልጣናት እስረኞቹ ሊያመልጡ የቻሉት በእስር ቤቱ ውስጥ ባለው ቸልተኝነት እና የብቃት ችግር ነው ብለዋል።

ሦስቱን እስረኞች መልሶ በቁጥጥር ሥር ለማዋል አገር አቀፍ ፍለጋ ተጀምሯል።

ባለሥልጣናት ሦስቱን ግለሰቦች መልሶ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥቆማ ለሚሰጥ 20 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ (ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ) በሽልማት መልክ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

ከእስር ያመለጠው ሁለተኛው ወንጀለኛ እአአ 2012 በኬንያ ፓርላማ ላይ ጥቃት ለማድረስ ታስቦ ሳይሳካ ከቀረው ሙከራ ጋር በተገናኘ የተያዘ ነው። ሦስተኛው ደግሞ በሶማሊያ በስፋት የሚንቀሳቀሰውን ጽንፈኛውን የአል-ሸባብ ቡድንን ለመቀላቀል ሲሞክር የተያዘ ግለሰብ ነው።

የኬንያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ፍሬድ ማቲያንጊ፤ "ሦስቱን ሰዎች ለመያዝ ሰፊ ፍለጋ እናካሂዳለን። አደገኛ ወንጀለኞች ናቸው። መያዝ አለብን" ካሉ በኋላ፤ "መሰል ቸልተኝነት ዳግም እንዳይከሰት በትክክል እናረጋግጣለን" ብለዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ እስረኞቹ ያመለጡበት ሁኔታን በመተመለከተ በፖሊስ የሚካሄደው ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጨማሪ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ከእስር ያመለጠው ሞሐመድ አሊ አቢካር ከሌሎች ሦስት ተባባሪዎቹ ጋር የ41 ዓመት እስር ተፈርዶበት በኪማቲ እስር ቤት ይገኝ ነበር።

እስረኞቹ ያመለጡበት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት ካሚቲ እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስረኞቹ ያመለጡበት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት ካሚቲ እስር ቤት

እአአ 2015 ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ጽንፈኞች የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥበቃዎችን ገድለው ከገቡ በኋላ በተማሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተው በርካቶችን ገድለዋል። የዓይን እማኞች በወቅቱ ክርስቲያን ተማሪዎች ተለይተው በጽንፈኛ ታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግረው ነበር።

የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥቃትን ያቀነባበረው ሞሐመድ ኩኖ እአአ 2016 ላይ በሶማሊያ ተገድሏል።

ይህ የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥቃት በኬንያ ታሪክ በሽብር ጥቃት በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ሁለተኛው ጥቃት ነው። እአአ 1998 ላይ አል-ቃይዳ በናይሮቢ በሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።